በክልሉ የሚገኙ የልማት ማህበራት የልማት ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚገኙ የልማት ማህበራት የልማት ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ ነው
ዲላ፤ መስከረም 12/2018(ኢዜአ):- በክልሉ የሚገኙ የልማት ማህበራት በመንግሥት ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ተግባራት እያከናወኑ መሆኑን የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ(ዶ/ር) ገለፁ።
ማህበራቱ የልማት ክፍተቶችን የመሙላት አቅማቸውን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ መሆኑንም አክለዋል።
የጌዴኦ ልማት ማህበር ጠቅላላ ጉባኤውን በዲላ ከተማ እያካሄደ ነው።
በጉባኤው በልማት ማህበሩ የተከናወኑ የልማት ስራዎች የመስክ ምልከታና የፎቶ አውደ ርዕይ የተካሄደ ሲሆን አባላትና አጋር አካላት እየተሳተፉ ነው።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በወቅቱ እንዳሉት፤ በክልሉ የሚገኙ የልማት ማህበራት በመንግሥት ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን በመለየት ውጤታማ ተግባር እያከናወኑ ነው።
በተለይ በትምህርት ልማት ስራዎች የትምህርት ስብራትን ለመጠገን የሚደረገውን ጥረት እያገዙ እንደሚገኝ አንስተው በዚህ ረገድ የጌዴኦ ልማት ማህበር የሚበረታታ ተግባራት እያከናወነ ነው ብለዋል።
ልማት ማህበሮች የመሰባሰብ ምልክት ናቸው ያሉት ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ክልሉ ያለውን እምቅ የማደግ አቅም በመጠቀም ረገድ ድርሻቸው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።
ለዚህም የገቢ አቅማቸውን በማሳደግና ህብረተሰቡን በማስተባበር የልማት ተሳትፏቸውን በማሳደግ በመንግሥት ያልተሸፈኑ የልማት ክፍተቶችን የመሙላት አቅማቸውን ለማጠናከር በትኩረት እየተሠራ ነው ብለዋል።
በዞኑ የልማት ማህበሩን አቅም በማጎልበት እያደገ ለመጣው የህዝብ የልማት ጥያቄ ምላሽ እየተሠጠ ነው ያሉት ደግሞ የጌዴኦ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ዝናቡ ወልዴ (ዶ/ር) ናቸው።
በተለይም በሠለጠነ የሰው ኃይል ልማት፣ በትምህርት መሠረተ ልማት ግንባታ፣ በግብርናና ጤና እንዲሁም በሃገራዊና ክልላዊ ኢንሼቲቮች በልማት ማህበሩ አበረታች ተግባራት መከናወናቸውን አንስተዋል።
በቀጣይም የልማት ማህበሩን የገቢ አቅምና የአጋር አካላትን ተሳትፎ በማጠናከር ለላቀ የዞኑ ሁለንተናዊ ልማት ለመጠቀም እንደሚሠራም ተናግረዋል።
የጌዴኦ ልማት ማህበር ስራ አስኪያጅ አቶ ብዙነህ ንጉሴ በበኩላቸው ማህበሩ ከግማሽ ሚሊዮን በላይ አካላትን በማቀፍና ሃብት በማሰባሰብ የተለያዩ የልማት ተግባራትን እያከናወነ መሆኑን ጠቅሰዋል።
በተለይም በትምህርት ልማት ተደራሽነት ከቅድመ አንደኛ እስከ አዳሪ ትምህርት ቤቶችን ገንብቶ ለአገልግሎት በማብቃት ከ10 ሺህ ለሚልቁ ተማሪዎች ምቹ የመማርያ ከባቢን መፍጠሩን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በተጨማሪም በግብርና፣ በኮሪደር ልማት፣ በጤናና በምንጭ ማጎልበት ለህዝብ ጥያቄ ምላሽ መሰጠቱንም አንስተዋል።
የልማት ማህበሩ የልማት ተሳትፎ አበረታች ቢሆንም እያደገ ከመጣው የልማት ጥያቄ አንፃር ብዙ መስራት እንደሚጠበቅ ጠቅሰዋል።
ለዚህም የውስጥ ገቢ አቅምን ከማሳደግ ባለፈ የአጋር አካላትን የላቀ ተሳትፎ የሚጠይቅ መሆኑን አንስተው ሁሉም ልማት ወዳዱ ማህበረሰብ የልማት ማህበሩ አባል እንዲሆንም ጠይቀዋል።
በጉባኤው የፌደራል፣ የክልል እና የዞኑ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች፣ ከተለያዩ ማህበራዊ መሠረት የተወጣጡ የልማት ማህበሩ አባላትና አጋር ተቋማት ተሳታፊ ሆነዋል።