መጪውን የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል -የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን - ኢዜአ አማርኛ
መጪውን የመስቀል ደመራ በዓል በድምቀት ለማክበር አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል -የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን
አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2018(ኢዜአ)፦ የ2018 የመስቀል ደመራ በዓል ሀይማኖታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ ማክበር የሚያስችል ዝግጅት መጠናቀቁን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ-ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ገለጹ።
ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የበዓሉን አከባበር አስመልክተው በሰጡት መግለጫ የመስቀል ደመራ በዓል የሰላም ምልክት የአንድነትና አብሮነት እሴትን የሚያጠናክር ነው ብለዋል፡፡
የመስቀል ደመራ በዓል ከኃይማኖታዊ አስተምህሮው ባሻገር የኢትዮጵያዊያን አንድነት፣ መተባበርና አብሮነት የሚገለጽበት መሆኑን ተናግረዋል።
በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ከሚከበሩ ሃይማኖታዊ የአደባባይ በዓላት አንዱ የመስቀል ደመራ በዓል መሆኑን ገልፀው፤ ምዕመናን ደመራ ደምረው ችቦ እያበሩ በዓሉን በሀይማኖታዊ ስርዓት እንደሚያከብሩም ጠቅሰዋል፡፡
በዓሉ የአንድነት፣ የፍቅር፣ የይቅርታ፣ አብሮነት፣ የምስጋናና የተስፋ እሴቶች የሚገለጹበት ኃይማኖታዊ ክብረ-በዓል ሲሆን፤ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች በደማቅ ሁኔታ ይከበራል ብለዋል።
በዚህም በዓሉ ሀይማኖታዊ ትውፊቱን ጠብቆ እንዲከበር ኮሚቴ በማዋቀር ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልፀዋል።
ምዕመናኑ በዓሉ ሀይማኖታዊ ስርዓቱን በጠበቁ መልኩ እንዲከበር የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡም የጠቅላይ ቤተክህነቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ ጥሪ አቅርበዋል።
ምዕመናን የመስቀሉን አስተምህሮ በመከተል የፍቅር ምሳሌ የሆነውን በዓል በአብሮነትና በጋራ ማክበር ይገባል ነው ያሉት ብፁዕነታቸው።