ቀጥታ፡

በሕብረት ያጠናቀቅነው ታላቁ የህዳሴ ግድብ ለነገው ትውልድ የምናስረክበው ደማቅ አሻራችን ነው - ከንቲባ ከድር ጁሃር

ድሬዳዋ፤ መስከረም 12/2018 (ኢዜአ)፦  በሕብረ ብሔራዊ አንድነት ለስኬት የበቃው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ   ለነገው ትውልድ የምናስረክበው ደማቅ አሻራችን ነው ሲሉ  የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር ተናገሩ።

በሕዳሴው ግድብ ላይ የታየው ከፍተኛ ርብርብ በሌሎች ሀገራዊና የአስተዳደሩ የልማት ፕሮጀክቶች ላይ መደገም እንደሚገባውም ከንቲባው አስገንዝበዋል።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቁን ተከትሎ በድሬዳዋ ከመስከረም 4 ቀን 2018ዓ.ም ጀምሮ ሲካሄድ የቆየው  የድጋፍና የደስታ ሰልፎችና ክዋኔዎች ዛሬ ደግሞ በአስተዳደሩ ደረጃ ተከናውኗል።


 

በሕዝባዊ ሰልፉ ላይ የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች፣ የፀጥታና የፍትሕ አካላት፣ የሀገር ሽማግሌዎችና ሌሎችም የሕብረተሰብ ክፍሎች ተገኝተዋል።

በሰልፉ ላይ የተሳተፉት የድሬዳዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃር፤ የሕዳሴው ግድብ ኢትዮጵያውያን በሕብረ ብሔራዊ አንድነትና ትብብር   የገነባነው ደማቅ አሻራችን  ነው ብለዋል።

ግድቡ ለኢትዮጵያ የብልጽግና ጉዞ መሳካት እና  ከፍታ ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰዋል።


 

ኢትዮጵያውያን ከተደመርን የትኛውንም ሀገራዊ ጉዳይ ከዳር ማድረስና ከተስፋ ወደሚጨበጥ ብርሃን መሸጋገር እንደምንችል በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሳይተናል ብለዋል።

በቀጣይም ይሕንኑ ፅናትና ሕብረ ብሔራዊ አንድነት በማጠናከር እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ድሬዳዋ አስተዳደር የተጀመሩ የልማት ፕሮጀክቶችን ከዳር ለማድረስ መረባረብ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።


 

ለሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ በድሬዳዋ የሚገኙ የሕብረተሰብ ክፍሎች ላደረጉት ከፍተኛ አስተዋፅኦና ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም