ቀጥታ፡

የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት የሰብስቴሽን ግንባታ እየተካሄደ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 12/2018 (ኢዜአ)፦የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት እና የተሳለጠ ኃይል እንዲያገኙ ለማስቻል የሰብስቴሽን ግንባታ እየተካሄደ መሆኑን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አስታወቀ።

የሰብስቴሽን ግንባታው ሙሉ በሙሉ ተጠናቆ በዚህ ዓመት አገልግሎት እንደሚሰጥም ተገልጿል።

በኢንዱስትሪ ዘርፍ የሚያጋጥሙ ችግሮች በጥናት ተለይተው በተቋማት የተቀናጀ ተግባር ምላሽ እንዲያገኙ ብሄራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል መቋቋሙ ይታወሳል።

በዚህም የኢንዱስትር ካውንስሉ በአዲስ አበባና ከአዲስ አበባ ውጪ በሚገኙ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች፣ አግሮ ኢንዱስትሪዎች፣የስጋ፣የመኖ ማቀነባበሪያና የሶላር ማምረቻ ፋብሪካዎች የመስክ ምልከታ አድርጓል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ ኢንጂነር አሸብር ባልቻ በዚሁ ወቅት ለኢዜአ እንደገለጹት የአግሮ ኢንዱስትሪዎችን የኤሌክትሪክ ኃይል ፍላጎት በዘላቂነት ለማሟላት እና የተሳለጠ ኃይል እንዲያገኙ ለማስቻል የሰብስቴሽን ግንባታ እየተካሄደ ነው።


 

ግንባታው ሲጠናቀቅ ከኃይል አቅርቦት ጋር ተያይዞ የሚነሳውን ችግር በመቅረፍ ኢንዱስትሪዎች ምርትና ምርታማነታቸው የበለጠ እንዲሳለጥ እንደሚያደርግ ጠቁመዋል።  

ግንባታውንም በተያዘው ዓመት ለማጠናቀቅ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ገልጸው፤ በቂ ኃይል በሌላቸው ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ሰብስቴሽኖች ላይ ተጨማሪ የማስፋፊያ ስራ እንደሚከናወንም ተናግረዋል።

ለኢንዱስትሪው አስፈላጊውን ኃይል በማቅረብ ምርትና ምርታማነት የበለጠ እንዲሳለጥ ተቋሙ የበኩሉን እንደሚወጣ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኢንጅነር ጌቱ ገረመው በበኩላቸው፤ በልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የአቅርቦት እና ከኃይል መቆራረጥ ጋር ተያይዞ ያሉ ችግሮች በሂደት ምላሽ እያገኙ መሆኑን ተናግረዋል።


 

እስከ አሁን ያሉት ችግሮች በሂደት እየተፈቱ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘላቂነትም ችግሩን ለመቅረፍ ከባለድርሻ አካላት ጋር በትብብር እየተሰራ ይገኛል ብለዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም