ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመደመር እና የወል እውነታን በተግባር ያሳየ ነው - ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመደመር እና የወል እውነታን በተግባር ያሳየ ነው - ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ሮዛ ኡመር
ሐረር ፤ መስከረም 12 /2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመደመር እና የወል እውነታን በተግባር ያሳየ ነው ሲሉ የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይዘሮ ሮዛ ኡመር ገለጹ።
"በህብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሐረሪ ክልል ታላቅ የድጋፍ ሰልፍ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በድጋፍ ሰልፉ ላይ የክልሉ ምክር ቤት አፈ ጉባዔ ሱልጣን አብዱሰላም እና በብልጽግና ፓርቲ የሐረሪ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ጌቱ ወዬሳን ጨምሮ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና በክልሉ በተለያዩ የገጠርና ከተማ ወረዳዎች የሚገኙ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች፤ የፀጥታ አካላት እና ሌሎች ተሳትፈዋል።
በሐረር ኢማም አህመድ ስታድየም ለተገኘው ህዝብ ንግግር ያደረጉት የሐረሪ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ወይወሮ ሮዛ ኡመር ባስተላለፉት መልዕክት የኢትዮጵያውያን አንድነት የታየበት ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ግንባታ በመጠናቀቁ እንኳን ደስ አላችሁ ብለዋል።
ግድቡ ለኢትዮጵያዊያን የዘመናት ቁጭት ምላሽ የሰጠና የመንፈስ ጥንካሬ የታየበት ታላቅ ገድል ነው ያሉት ወይዘሮ ሮዛ፤ ግድቡ የመደመርና የወል እውነታን በተግባር ያሳየ የሁላችንም ኩራት ነው ብለዋል።
በህብረት እውን ያደረግነው ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የማንሰራራት ዘመን ማሳያ ተደርጎ የሚወሰድ የሉአላዊነታችን ግርማ ሞገስ፤ የብሄራዊ ኩራታችን ምንጭ፤ የአንድነታችን ካባ ምልክት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ስንተባበር ሁሉን ማሳካት እንደምንችል የሚያሳይና የትጋት ውጤት ነው ሲሉም ተናግረዋል።
የህዳሴ ግድቡ መመረቅ በራስ አቅምና በጋራ መስራት እንደምንችል ለሌላው አለም ያሳየንበትና ለቀጣይ የልማት ስራዎች አስተዋጽኦ እንድናጎለብት መነሳሳትን የፈጠረ ነው ብለዋል።