ቀጥታ፡

ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ትብብር ይበልጥ አጠናክራ መቀጠል ትፈልጋለች

አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2018 (ኢዜአ)፡- ኮሎምቢያ ከኢትዮጵያ ብሎም ከአፍሪካ ጋር በተለያዩ የትብብር ዘርፎች ያላትን ግንኙነት ይበልጥ አጠናክራ ለመቀጠል ቁርጠኛ መሆኗን አስታወቀች።

ከኢትዮጵያ ብሎም ከአፍሪካ ጋር የጠበቀ ግንኙነት መፍጠር ለኮሎምቢያ የላቀ ፋይዳ እንዳለው በኢትዮጵያ የሀገሪቱ አምባሳደር የሴን አርኬዲዮ ሜኔሰስ ኮፕቴ ለኢዜአ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ ቡናን ጨምሮ በተለያዩ ዘርፎች በትብብር እየሠሩ መሆናቸውንም አውስተዋል።

ኮሎምቢያ ከአፍሪካ ጋር ለምታደርገው የንግድና ሌሎች ግንኙነቶች የአኅጉሩ ኩራት የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወሳኝ ድልድይ መሆኑንም ተናግረዋል።

ዓለምን ከአፍሪካ ከሚያገናኘው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በተያያዘ የተጀመሩ ሥራዎች መኖራቸውን እና በቀጣይም ተስፋፍተው የሚቀጥሉ አሠራሮች እንዳሉም አመላክተዋል።

የአየር መንገድ ትሥሥርን ማጠናከር የቢዝነስ ዘርፎችን ለማሳደግ እና የወጪና ገቢ ንግድን ለማሳለጥ ቁልፍ ጉዳይ መሆኑንም አስረድተዋል።

አምባሳደሩ አክለውም፤ ከንግድና ትራንስፖርት ባለፈ ግብርና፣ ትምህርት እና ቱሪዝም በሀገራቱ መካከል የትብብር መስኮች ተደርገው መወሰዳቸውን ተናግረዋል።

የሰው ዘር መገኛ ከሆነችው እና በበርካታ መስኅቦች ከታደለችው ኢትዮጵያ ጋር በቱሪዝም ዘርፍ በትብብር መሥራት አስፈላጊ መሆኑንም አንስተዋል።

ኮሎምቢያ በቅርቡ በአዲስ አበባ ኤምባሲዋን በድጋሚ መክፈቷ ከኢትዮጵያ ጋር ያላትን ግንኙነት ለማጠናከር የጀመረችውን ቁርጠኝነት ያሳያል ያሉት አምባሳደሩ፤ ከአፍሪካ አኅጉር ጋር ለሚኖራት ግንኙነትም እንደ መግቢያ በር ይሆናል ነው ያሉት።

የሁለቱ ሀገራት ተወካዮችን ያሳተፈ ከፍተኛ የቢዝነስ ፎረም በአዲስ አበባ መካሄዱን አውስተው፤ ፎረሙ የግሉ ሴክተር ትብብር አዳዲስ መንገዶችን ለመፈተሽ እና የሁለትዮሽ ኢኮኖሚያዊ ትስስሩን ለማጠናከር ዕድል ሰጥቷል ብለዋል።

ሁለቱ ወገኖች በተለያዩ ዘርፎች የወደፊት አጋርነትን ስለመፍጠር ያላቸውን ተስፋም መግለጻቸውን ጠቅሰዋል።

ኢትዮጵያ እና ኮሎምቢያ ከ1947 ጀምሮ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመራቸው ይታወቃል።

በዚሁ መሠረትም ኮሎምቢያ በ1967 ኤምባሲዋን በአዲስ አበባ መክፈቷ እና በ1974 ተዘግቶ ነሐሴ 21 ቀን 2017 ዓ.ም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ (ዶ/ር) እና የኮሎምቢያ ምክትል ፕሬዚዳንት ፍራንሲያ ማርኩዌዝ በተገኙበት እንደገና መከፈቱ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም