ቀጥታ፡

ሠራዊቱ ዘመኑን በሚመጥን ስልጠና ውስጥ በማለፍ የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል - ጄነራል ይመር መኮንን

ሁርሶ፣ መስከረም 11/2018(ኢዜአ)፦ ሠራዊቱ ዘመኑን በሚመጥን ስልጠና ውስጥ በማለፍ የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል ሲሉ የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄነራል ይመር መኮንን ተናገሩ።

በመከላከያ ሚኒስቴር የትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ የሁርሶ ዕጩ መኮንን ማሰልጠኛ ትምህርት ቤት ዕጩ መኮንኖችን ዛሬ አስመርቋል።


 

የመከላከያ ትምህርትና ስልጠና ዋና መምሪያ ኃላፊ ጄነራል ይመር መኮንን በዚሁ ወቅት እንዳሉት የሀገር መከላከያ ሠራዊት ዘመኑን በሚመጥን ስልጠና ውስጥ በማለፍ የሀገርን ሉዓላዊነት በአስተማማኝ መንገድ የመጠበቅ ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል።

የብሔራዊ ጥቅማችን ማረጋገጫ የሆነው የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ሌሎች በቀጣይ የሚከናወኑ ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች የኢትዮጵያን ከፍታ የሚመልሱና የሠራዊቱንም መሠረት በላቀ ደረጃ የሚያፀኑ መሆናቸውን ገልፀዋል።

ሠራዊቱ ብሔራዊ ጥቅሞቻችንን ለማስከበር ከመቼውም ጊዜው በላይ በመሰልጠን፣ በመደራጀትና በመታጠቅ የትኛውንም መስዋዕትነት ለመክፈል ተዘጋጅቷልም ብለዋል።

ለዚህ እውን መሆን ፕሮፌሽናል አመራሮችና ባለሙያዎች በየመስኩ እየሰለጠኑ መሆኑን ጠቅሰው፤ በዘመናዊ እውቀትና በቴክኖሎጂ የታገዘ ዘመኑን የሚመጥን ለሁሉም ግዳጅ ዝግጁ የሆነ ሰራዊት መገንባቱንም ገልጸዋል።


 

ዛሬ የተመረቁት የንስር ኮርስ ዕጩ መኮንኖች በቆይታቸው የትኛውንም ሀገራዊ ግዳጅ በታላቅ ብቃት መወጣት የሚያስችላቸው የቴክኒክ፣ የአመራር፣ የንድፍና የተግባር ስልጠና እንደተሰጣቸው የገለፁት ደግሞ የትምህርት ቤቱ አዛዥ ኮሎኔል ከድር ጫንጮ ናቸው።

በሀገራችን የሰላም፣ የልማት እና የዴሞክራሲ መንገዶች በአስተማማኝና አመርቂ በሆነ መንገድ እየተካሄዱ መሆናቸውን ገልፀው እነዚህ በላቀ ደረጃ እንዲያብቡ ሠራዊቱ ኃላፊነቱን በቁርጠኝነት ይወጣል ብለዋል።

የዛሬዎቹ ተመራቂዎችም ለመከላከያ ሠራዊቱ ትልቅ አቅምን የሚፈጥሩ መሆናቸውን ጠቅሰው በቀጣይም ከፍተኛ ወታደራዊ ስነ-ምግባር በመላበስ አገራዊ ኃላፊነታቸውን በላቀ ብቃት እንዲወጡም አመላክተዋል።


 

በምረቃ ስነ-ስርዓቱ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ፣ የመከላከያ መረጃ ዋና መምሪያ ሃላፊ ጄነራል ጌታቸው ጉዲና እና የኢፌዴሪ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጄነራል ይልማ መርዳሳን ጨምሮ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች፣ የድሬደዋ አስተዳደር ከንቲባ ከድር ጁሃርና ሌሎች እንግዶች ተገኝተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም