የህዳሴው ግድብ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ የመቆማችን ውጤት ነው - ኢዜአ አማርኛ
የህዳሴው ግድብ ለብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ የመቆማችን ውጤት ነው
ቦንጋ፤ መስከረም 11/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ተጠናቆ ለፍሬ መብቃቱ የፖለቲካ ልዩነቶች ሳይገድቡን ለብሔራዊ ጥቅም መከበር በጋራ የመቆማችን ውጤት ነው ሲሉ የኢትዮጵያ የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ ገለፁ።
ህዳሴን ገንብተን ለጥቅም እንዳበቃነው ሁሉ የባህር በር ባለቤትነት ላይም መረባረብ እንደሚገባም ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ያለልዩነት የተረባረብንበትና ለፍፃሜ ያበቃነው የጋራ ሀብታቸው ነው።
የህዳሴው ግድብ ግንባታን አስመልክተው አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡት የካፋ አረንጓዴ ፓርቲ ፕሬዚዳንትና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢ አቶ ሰለሞን አየለ እንዳሉት፣ ግድቡ የአንድነትና የትብብር ውጤት ነው።
ግድቡ አንድ ከሆንና ከተባበርን ከራሳችን አልፎ ለሌሎችም መብቃት እንደምንችል ምሳሌ መሆኑን ጠቅሰው፤ በራሳችን ገንዘብ፣ እውቀትና ጊዜ መጨረስ መቻላችን ደግሞ ትልቁ የከፍታችን ተምሳሌት ነው ብለዋል።
ለግድቡ ግንባታ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሊቅ እስከ ደቂቅ ልዩነቶች ሳይገድበን ያሳየነው የትብብር ውጤት መሆኑን ጠቅሰው በተባበረ ክንድ የፈጸምነው ዳግማዊ ዓድዋችን ነውም ብለዋል።
በቀጣይም ዓባይ ላይ ህዳሴን በመገንባት የጋራ ሀብታችን እንዳደረግነውና ለጥቅም እንዳበቃነው ሁሉ የባህር በር ባለቤትነት ላይም በአብሮነትና በአንድነት በመቆም እውን እንዲሆን መረባረብ አለብን ሲሉ ተናግረዋል።
በዚህ ረገድ ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች የባህር በር ባለቤትነት ላይ ፅኑ አቋም እንዳላቸው ያነሱት አቶ ሰለሞን፣ በህዳሴው ግድብ ያሳየነውን አቅምና አቋም ማጠናከር ይጠበቅብናልም ብለዋል።
ያለን አንድ ሀገር በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ፓርቲዎች በሀገር ልማት፣ ሉዓላዊነትና ብሔራዊ ጥቅም ላይ አብሮ መቆም የህልውና ጉዳይ መሆኑን አፅንኦት ሰጥተዋል።