ቀጥታ፡

በህዳሴ ግድብ ያሳየነውን የመቻልና የመፈፀም አቅም በሌሎች የልማት ዘርፎችም እንደግማለን - ርዕሰ  መስተዳድር አወል አርባ

ሰመራ፤ መስከረም 11/2018(ኢዜአ)፦ በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ያሳየነውን የመቻልና የመፈፀም አቅም በሌሎች የልማት ዘርፎችም እንደግማለን ሲሉ የአፋር ክልል ርዕሰ  መስተዳድር አወል አርባ ተናገሩ።


 

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን ተከትሎ በአፋር ክልል በተለያዩ ወረዳዎች ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍና የደስታ መግለጫ ትዕይንተ ህዝብ ዛሬ ተካሄዷል።


 

በሰመራ በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የተገኙት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አወል አርባ በህዳሴ ግድብ ያሳየነውን የመቻልና የመፈፀም ተግባራችንን በተለያዩ የልማት ዘርፎችም እናስቀጥላለን ብለዋል።

የህዳሴ ግድብ ሀገራችን የጀመረችውን መጨረስ እንደምትችልና አሸናፊ መሆኗን ያስመሰከረችበት፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊያን አሻራ ያረፈበት ዳግማዊ ዓድዋ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልጸዋል።

የህዳሴ ግድብ ለእኛ ለኢትዮጵያውያን ብቻ ሳይሆን ለአፍሪካውያን የብርሃን ተስፋን ያሳየ፣ የቀጣናው መተሳሰር የተጠናከረበት የወል ትርክታችን ህያው ምስክር ነው ሲሉም ተናግረዋል።


 

የሰመራ ሎጊያ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አብዱ ሙሳ በበኩላቸው ግድቡ እኛ ኢትዮጵያውያን በይቻላል መንፈስ ጠንክረን ከሰራን ሌሎች ልማቶችንም ማሳካት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል።


 

በሠመራ ስታዲየም በተካሄደው የድጋፍ ሰልፍ ላይ ልዩ ልዩ ትርዒቶችና ባህላዊ ጭፈራዎች የቀረቡ ሲሆን የህዳሴን ግድብና የትብብር ስኬትን የሚያሳዩ መልዕክቶችም በመፈክር መልክ ቀርበዋል።

በድጋፍ ሰልፉ ላይ የአፋር ክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም