ኢትዮጵያ በሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዋን ከኬንያ ጋር ዛሬ ታደርጋለች - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ በሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታዋን ከኬንያ ጋር ዛሬ ታደርጋለች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 11/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከ20 ዓመት ሴቶች ብሄራዊ ቡድን የዓለም ዋንጫ ማጣሪያ የመጀመሪያ ጨዋታውን ዛሬ ከኬንያ አቻው ጋር ያደርጋል።
የሁለቱ ሀገራት ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
የብሄራዊ ቡድኑ አሰልጣኝ ቻለው ለሜቻ ለጨዋታው ዝግጅት ለ33 ተጫዋቾች የመጀመሪያ ዙር ጥሪ በማድረግ ለሁለት ሳምንታት ገደማ ቡድኑ ልምምዱን ሲያደርግ ቆይቷል።
ከጊዜያዊ ስብስቡ ዓይናለም ዓለማየሁ፣ ቅድስት ጤቃ፣ ሸዊት አብርሃ፣ ህዳት ካሱ፣ ቤዛዊት ንጉሴ፣ ባዩሽ ኪንባ እና ፅግነሽ አዴ ሲቀነሱ ትዕግሥት ወርቄ እና ምትኬ ብርሀኑ በጉዳት ከስብስቡ ውጪ ሆነው በ24 ተጫዋቾች የመጨረሻ ቀናት ልምምዱን አከናውኗል።
በጃክሊን ጁማ የሚመራው የኬንያ ከ20 ዓመት በታች ሴቶች ብሄራዊ ቡድን 23 ተጫዋቾችን በመያዝ ዝግጅቱን አድርጓል።
ሁለቱ ሀገራት እ.አ.አ በ2017 በዘጠነኛው የፊፋ ከ20 ዓመት በታች የሴቶች ዓለም ዋንጫ ለማለፍ የአፍሪካ ዞን ማጣሪያ ተገናኝተው ኬንያ በድምር ውጤት 4 ለ 3 ማሸነፏ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ እና ኬንያ የመልስ ጨዋታቸውን መስከረም 18 ቀን 2018 ዓ.ም በናይሮቢ ያደርጋሉ።
ሉሲዎቹ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፉ በሶስተኛው ዙር ከታንዛንያና አንጎላ አሸናፊ ጋር ይጫወታሉ።
በፖላንድ አስተናጋጅነት እ.አ.አ በ2026 ለሚካሄደው 12ኛው የሴቶች ከ20 ዓመት በታች የዓለም ዋንጫ 24 ሀገራት ይሳተፋሉ።
አፍሪካ በውድድሩ ላይ አራት ሀገራት የማሳተፍ ኮታ ያገኘች ሲሆን ሀገራት በአራት ዙር የማጣሪያ ጨዋታቸውን እንደሚያደርጉ የአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) አስታውቋል።