የሕዳሴ ግድብን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ - ኢዜአ አማርኛ
የሕዳሴ ግድብን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ዝግጅቱ ተጠናቋል - ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ
ዱራሜ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን የቱሪዝም ሚንስትር ሰላማዊት ካሳ አስታወቁ።
የቱሪዝም ሚኒስትር ሰላማዊት ካሳ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የተለያዩ የቱሪስት መስሕብ ስፍራዎችን ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
ከጉብኝታቸው በኋላ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት ማብራሪያ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ የተቀናጀ ዝግጅት ሲደረግ መቆየቱን አንስተዋል።
የሕዳሴው ግድብ ግንባታ በስኬት መጠናቀቅን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር)፤ ለጎብኚዎች ክፍት እንደሚደረግ በተናገሩት መሰረት የዝግጅት ስራ መከናወኑን ገልጸዋል።
በዚህም መሰረት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን ለጎብኚዎች ክፍት ለማድረግ ዝግጅቱ መጠናቀቁን አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ አየር መንገድ በሳምንት ሁለት በረራዎችን በማድረግ ጉብኝቱ የሚጀመር መሆኑንም ሚንስትሯ አረጋግጠዋል።
ሚኒስትሯ በማብራሪያቸው ታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አስደናቂ ፕሮጀክት ለመጎብኘት የሚሹ ሁሉ በተለያዩ አማራጮች በሚቀመጡ አድራሻዎች መመዝገብ የሚችሉ መሆኑንም ጠቁመዋል።
የሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ ጳጉሜን 4/2017 ዓ.ም ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ጋር የተለያዩ ሀገራት መሪዎች በተገኙበት መመረቁ ይተወሳል።