የመከላከያ ሠራዊት አሁናዊ ቁመና እና ዝግጁነት የኢትዮጵያን ህልውና ለማይሹ አካላት ትልቅ መልዕክት የሚሰጥ ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ - ኢዜአ አማርኛ
የመከላከያ ሠራዊት አሁናዊ ቁመና እና ዝግጁነት የኢትዮጵያን ህልውና ለማይሹ አካላት ትልቅ መልዕክት የሚሰጥ ነው -ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ የመከላከያ ሠራዊት አሁናዊ ቁመና እና ዝግጁነት የኢትዮጵያን ህልውና ለማይሹ አካላት ትልቅ መልዕክት የሚሰጥ ነው ሲሉ ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ ገለጹ።
ፕሬዝዳንት ታዬ አፅቀሥላሴ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አቅራቢነት ከፍተኛ የጦር መኮንኖችን ሾመዋል።
ፕሬዝዳንቱ በዚሁ ጊዜ ባስተላለፉት መልዕክት፣ ሹመቱ ከፍተኛ መኮንኖች ላሳዩት የስራ ጥንካሬ፣ ታማኝነትና ብርታት የተሰጠ ነው ብለዋል።
ውትድርና ለሀገር ሉዓላዊነት እና ለህዝብ ክብር ህይወትን አሳልፎ ለመስጠት ቃል ኪዳን የሚገባበት ታላቅ ሙያ መሆኑንም ገልጸዋል።
የጽኑ ወታደር ቋንቋው ሀገርና ህዝብን ማገልገል መሆኑን ጠቅሰው፣ የመከለከያ ሠራዊቱም በዚህ ረገድ ከመቼውም ጊዜ በላይ ዝግጁ መሆኑን ተናግረዋል።
የሠራዊቱ አሁናዊ ዝግጁነት የኢትዮጵያን ህልውና ለማይሹ አካላት ትልቅ መልዕክት የሚሰጥ መሆኑንም አብራርተዋል።
የኢፌዴሪ መከላከያ ሠራዊት መልህቁ በሁሉም አግባብ ራስን መቻል እንዲሁም በቴክኖሎጂና ክህሎት ልቆ መገኘት መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
ይህም የኢትዮጵያን ህላዊ ለማወክ በጋሻ ጃግሬነት ለመሰለፍ የሚከጅሉ ቡድኖች ባለቡት አካባቢ ትልቅ መድህን ነው ብለዋል።
የመከላከያ ሠራዊትን ዘመኑ ከደረሰበት ቴክኖሎጂ አስማምቶ የማይደፈር እንዲሆን ቀን ከሌት ለሰሩ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።
የኢትዮጵያ መንገድ ሰላም፣ ልማትና ብልጽግና መሆኑን የተናገሩት ፕሬዝዳንት ታየ አፅቀሥላሴ ፣ ይህን መንገድ ለማደናቀፍ የሚሹ አካላት ደግመው ደጋግመው ሊያስቡ ይገባል ሲሉም አስገንዝበዋል።