ቀጥታ፡

የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በመፍታት የዘርፉን የኢኮኖሚ ድርሻ ከፍ ለማድረግ ሥራዎች ተጠናክረው ቀጥለዋል

ሀዋሳ ፤መስከረም 10/2018  (ኢዜአ)፡-በሀገሪቱ የአምራች ኢንዱስትሪውን ማነቆዎች በመፍታት ዘርፉ በሀገር ኢኮኖሚ ላይ ያለውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ሥራዎች ተጠናክረው መቀጠላቸውን የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አስታወቀ።

ብሔራዊ የአምራች ኢንዱስትሪ ካውንስል በይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ እና በሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን የመስክ ምልከታ አድርጓል፡፡



 

የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር የመሠረተ ልማትና የግብዐት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሀሰን መሀመድ ካውንስሉ የተለያዩ ዘርፎችና ተቋማትን ያካተተ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡

የመስክ ምልክታው በአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ያሉ ማነቆዎችን በግንባር ቀርቦ ለመለየትና ከሚመለከታቸው ተቋማት ጋር በመቀናጀት የሚፈቱበትን መንገድ ለማመቻቸት እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በአምራች ኢንዱስትሪው የሚስተዋሉ የኃይል፣ የፋይናንስ አቅርቦት እና ሌሎች ማነቆዎች በመፍታት ዘርፉ በሀገር የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ላይ ያለውን ድርሻ ከፍ ለማድረግ የሚከናወኑ ተግባራት ተጠናክረው መቀጠላቸውን አንስተዋል፡፡

ይህንን ለማሳካት ከሚያስችሉ ሁኔታዎች መካከል በአሁኑ ወቅት በመንግስት ለዘርፉ የተሰጠው ልዩ ትኩረት ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀው፣ በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮች በአሁን ወቅት መፍትሔ እያገኙ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡    

አምራች ኢንዱስትሪው በተኪና በኤክስፖርት ምርት እንዲሁም በሥራ ዕድል ፈጠራ ላይ ትኩረት እንዲያደርግ ከመደረጉ ባለፈ ከክልሎችና ከባለሀብቶች ጋር በቅርበት በመስራት ተጨባጭ ለውጥ ለማምጣት መቻሉንም አቶ ሀሰን ገልጸዋል።

እንደሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ በአሁን ወቅት በተለይ የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርኮች እያሳዩ ያሉት እመርታ አበረታች ነው።

ፓርኮቹ ለሀገር እንዲሁም ለአካባቢው ማህበረሰብ እያበረከቱ ያሉትን አስተዋጾ በቀጣይ ለማሳደግ ሁሉን አቀፍ ድጋፍ እየተደረገላቸው መሆኑንም አስረድተዋል፡፡


 

የሲዳማ ኢንዱስትሪ ፓርኮች ልማት ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ኃይሉ የቴራ የካውንስሉ ምልከታ ያሉብንን ችግሮች በጋራ በመፍታት ቀልጣፋ አገልግሎት ለመስጠትና አምራች ኢንዱስትሪዎችም ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮላቸው ሥራቸውን ይበልጥ እንዲያሳድጉ የሚያስችል ነው ብለዋል፡፡

የካውንስሉ አባላት በተለይ በይርጋዓለም የተቀናጀ የግብርና ኢንዱስትሪ ፓርክ እየመጡ ያሉ ለውጦችና መፍትሄ የሚሹ ጉዳዮች ላይ መወያየታቸውን ጠቁመው፣ ማነቆ የሆኑ  ችግሮችን ለመፍታት አቅጣጫ መቀመጡን ጠቅሰዋል፡፡

የሀዋሳ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ባለሀብቶች ማህበር ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ ህብረት ለማ በበኩላቸው "ካውንስሉ ላሉብን የተለያዩ ችግሮች መፍትሄ በመስጠት መነቃቃትን እየፈጠረልን ነው" ብለዋል፡፡


 

ከዚህ በፊት የነበረው የኤክስፖርተሮች የዶላር አጠቃቀም ፖሊሲ በመቀየሩ ለባለሀብቱ ምቹ ሁኔታን መፍጠሩንም አመልክተዋል፡፡

በኢኮኖሚ ዞኑ የኃይል አቅርቦት እጥረት እንዳይከሰት ተጨማሪ የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት መኖሩ ምርታማነትን ለማሳደግ ጉልህ ሚና እንዳለውም አመልክተዋል።

በመስክ ምልከታው ላይ የጠቅላይ ሚኒስትሩ የማክሮ ኢኮኖሚ አማካሪና የካውንስሉ ሰብሳቢ አምባሳደር ግርማ ብሩ፣ የኢንዱስትሪ ሚኒስትሩ መላኩ አለበል፣ የግብርና ሚኒስቴሩ አዲሱ አረጋ እንዲሁም ሌሎች የካውንስሉ አባል ተቋማት ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል፡፡

 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም