የአቪየሽን ኢንዱስትሪውንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን የዋጀ የሰው ኃይል ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ - ኢዜአ አማርኛ
የአቪየሽን ኢንዱስትሪውንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን የዋጀ የሰው ኃይል ግንባታ ተጠናክሮ ይቀጥላል - ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የአቪየሽን ኢንዱስትሪውንና የቴክኖሎጂ ዕድገትን የዋጀ የሰው ኃይል ግንባታን አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአየር መንገዱ የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ ገለፁ።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ በበረራ፣ በአውሮፕላን ጥገና፣ በበረራ አስተናጋጅነትና በሌሎች የሙያ ዘርፎች ያሠለጠናቸውን 1 ሺህ 103 ተማሪዎችን አስመርቋል።
ከተመራቂዎች መካከል ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ 54 ሰልጣኞችም ይገኙበታል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ የቦርድ ሰብሳቢና የኢትዮጵያ አየር ኃይል ዋና አዛዥ ሌተናል ጀነራል ይልማ መርዳሳ፥ ተመራቂዎች አየር መንገዱ እያስመዘገበ ያለውን የከፍታ ጉዞ ለማስቀጠል በትኩረት ሊሰሩ ይገባል ብለዋል።
አየር መንገዱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቀዳሚ ለመሆን የሚያከናውናቸውን ተግባራት ለማፋጠን የሰው ሃብት ልማት ላይ እየሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።
ኢትዮጵያ በማንሰራራት ዘመን ላይ ትገኛለች ያሉት ሌተናል ጀኔራል ይልማ መርዳሳ በቅርቡ የሚገነባው ግዙፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሲጠናቀቅ በርካታ የተማረ የሰው ኃይል እንደሚፈልግ ጠቅሰዋል።
የአቪየሽን ቴክኖሎጂ ፈጣንና ተለዋዋጭ በመሆኑ ተመራቂ ተማሪዎች ራሳቸውን በየጊዜው ከአዳዲስ ቴክኖሎጂዎች ጋር ማስተዋወቅ እንደሚገባቸውም አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ አየር መንገድ ዋና ስራ አስፈፃሚ መስፍን ጣሰው በበኩላቸው አየር መንገዱ በአፍሪካና በዓለም ተመራጭና አስተማማኝ የበረራ ተቋም መሆኑን ተናግረዋል።
አየር መንገዱ በሁሉም መስክ ስኬታማ ሥራ በማከናወኑም በዓለም አቀፍ ደረጃ ተከታታይ እውቅናዎችን እያገኘ ነው ብለዋል።
በየዓመቱ በሺዎች የሚቆጠሩ ብቁ ሙያተኞችን በማሰልጠን የአህጉሪቱን የበረራ ኢንዱስትሪ በማሳደግ በኩል መሪ ሚናውን አጠናክሮ እየቀጠለ መሆኑንም አረጋግጠዋል።
ተመራቂዎች በዓለም ግዙፍ የሆነውን የኢትዮጵያ አየር መንገድ በመቀላቀላቸው የሚያኮራቸው መሆኑን በማንሳት፥ ኢንዱስትሪው በየጊዜው የሚፈልገውን አዳዲስ እውቀትና ክሕሎት አዳብረው መገኘት እንደሚጠበቅባቸው አስረድተዋል።
በበረራ መስተንግዶ የትምህርት ክፍልና በአውሮፕላን ጥገና ዘርፍ ከፍተኛ ውጤት በማምጣት የዋንጫ ተሸላሚ የሆኑት ተመራቂዎች ፍራኦሊ በቀለ እና መርአዊ ብርሃኑ በተሰጣቸው ስልጠና ትልቅ እውቀት አካብተናል ብለዋል።
አየር መንገዱ ግዙፍና የአፍሪካውያን ኩራት በመሆኑ በትምህርት ቆይታቸው የቀሰሙትን እውቀት በመጠቀም ለላቀ ስኬቱ የበኩላቸውን ሚና ለማበርከት መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል።