የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለሀገራችን ከፍታ በሙያችን እንድንተጋ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሮልናል - ተመራቂ ተማሪዎች - ኢዜአ አማርኛ
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ ለሀገራችን ከፍታ በሙያችን እንድንተጋ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሮልናል - ተመራቂ ተማሪዎች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ ለሀገራችን ዕድገትና ከፍታ በየሙያ መስካችን በትጋት እንድንሰራ ትልቅ መነሳሳትን ፈጥሮልናል ሲሉ የአዲስ አበባ የቴክኒክና ሙያ ተመራቂዎች ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች 7ሺህ 149 ተማሪዎቻቸውን በሚሊኒየም አዳራሽ አስመርቀዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂ ተማሪዎች ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁ ትልቅ ሀሴት እንደፈጠረባቸው ገልጸዋል።
ከምንም በላይ የይቻላልና የትጋት መንፈስ ፈጥሮልናል ያሉት ተመራቂዎቹ፥ በትምህርትና ስልጠና ቆይታቸው ያገኙትን ክህሎት እና እውቀት በመጠቀም የተሻለ ስራ ለመስራት እንዳነሳሳቸው ገልፀዋል።
ከተመራቂዎቹ መካከል ኪሩቤል ሞላ የሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ መመረቁ የኤሌክትሪክ አቅርቦት ችግርን በዘላቂነት የሚፈታ መሆኑ ለሚሰማራበት የዌብሳይት ዴቨሎፕመንት ሥራ ምቹ ዕድል ይፈጥራል ብሏል።
ኢትዮጵያ በብዙ መንገድ እያደገችና እየተለወጠች እንደምትገኝ የገለጸችው የዳታ ቤዝ አስተዳደር ተመራቂዋ ትዝታ ሽመልስ፥ የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅ በሙያችን ለሀገራችን ከፍታ እንድንተጋ ትልቅ ጉልበት ይሆነናል ነው ያለችው።
በኮንስትራክሽን ዘርፍ የተመረቀው አንተነህ ጉዬ በበኩሉ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኃይል ማመንጨት መጀመሩ ግብዓቶችን ለማምረትና የግንባታ ሥራዎችን በጥራትና በፍጥነት ለማጠናቀቅ ትልቅ አቅም መሆኑን ተናግሯል።
የግድቡ ሥራ መጀመር የኤሌክትሪክ አገልግሎት ተደራሽነትን ለማስፋትና የኃይል መቆራረጥን በማስቀረት በሁሉም መስክ ውጤታማ ለመሆን ያስችላል ያለችው በሆቴልና ቱሪዝም ዘርፍ የወርቅ ሜዳልያ ተሸላሚዋ ሐና ሻምበል ናት።