ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆምን የትኛውንም የልማት ፕሮጀክት ማሳካት እንደምንችል የሕዳሴ ግድቡ ማረጋገጫ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያዊያን በአንድነት ከቆምን የትኛውንም የልማት ፕሮጀክት ማሳካት እንደምንችል የሕዳሴ ግድቡ ማረጋገጫ ነው
ቦንጋ፤ መስከረም 10/2018 (ኢዜአ)፡- ኢትዮጵያውያን በአንድነት ከቆምን የትኛውንም የልማት ፕሮጀክት ማሳካት እንደምንችል የሕዳሴው ግድብ ስኬት ማረጋገጫ ነው ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የሀገር ሽማግሌዎችና የሀይማኖት አባቶች ገለጹ።
ኢትዮጵያዊያን ከጥንት ጀምሮ የሀገራቸውን ስምና ክብር ከፍ የሚያደርጉ ስራዎችን በማከናወን ደማቅ ታሪክ ሰርተዋል።
የአባቶቹን ፈለግ የተከተለው የዛሬው ትውልድም የማይደፈር በሚመስለው ዓባይ ላይ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብን በመገንባት የቁጭት ዘመን እንዲያበቃ አድርጓል።
የግድቡ ግንባታ ተጠናቆ በመመረቁም በመላ ሀገሪቱ ሕዝቡ ደስታውን እየገለጸ ይገኛል።
በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል የግድቡን ግንባታ ስኬት አስመልክተው አስተያየታቸውን የሰጡ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዋች፤ ኢትዮጵያውያን አንድ ከሆንንና ከተባበርን ማንኛውንም የልማት ፕሮጀክት ጀምረን መፈጸም እንደምንችል ግድቡ ማረጋገጫችን ነው ብለዋል።
ከአስተያየት ሰጪዎቹ መካከል ሊቀጠበብት ቀለመወርቅ አጥናፉ እንደገለጹት፤ የዓባይ ወንዝ ለልማት ሳይውል ዘመናት ማስቆጠሩ በህዝብ ላይ ቁጭት አሳድሮ ቆይቷል።
ግድቡን አልምቶ ሀብቱን ለጋራ ጥቅም ለማዋል ኢትዮጵያዊያን የተባበር ክንድ በማሳየታቸውና በአመራር ቁርጠኝነት የተለያዩ ፈተናዎችን በመቋቋም ለስኬት ለማብቃት መቻሉን ገልጸዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያዊያን የአብሮነት ማሳያ መሆኑን ገልጸው፣ የግድቡ መጠናቀቅ በቀጣይ ትብብር ካለ የትኛውንም የልማት ፕሮጀክት ማሳካት እንደሚቻል ማሳያ ነው ብለዋል።
የእንችላለን መንፈስን በሕብረተሰቡ ውስጥ እንዲሰርጽ ማድረጉንም ተናግረዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በአንድነት ከቆምን በልማትም ሆነ በሰላም የማናሳከው ነገር እንደሌለ አሳይቶናል ያሉት ደግሞ ሁስታዝ ሽኩር ጃፈር ናቸው።
"በተለያዩ ችግሮች ውስጥ በጋራና በሕብረት ለአንድ ዓላማ በመቆማችን የማይቻለውን ችለናል" ያሉት ሁስታዝ ሽኩር፣ በቀጣይም ከሕዳሴው ግድብ ትምህርት በመውሰድ ለሀገር የልማት ጉዞ መፋጠን መረባረብ ይገባናል ብለዋል።
የካፋ የሀገር ሽማግሌ ኮላዎቾቺ ግርማ ኪዳኔ በበኩላቸው፤ የሕዳሴው ግድብ ስንተባበር እንደሀገር መቆምና ልማትን ማፋጠን እንደምንችል በተጨባጭ ያሳየን የጋራ ቅርሳችን ሲሉ ገልጸዋል።
እንደ ሕዝብ ለልማት ያሳየነውን ድጋፍ በማጠናከር በቀጣይም በሌሎች የልማት ሥራዎች ላይ አጠናክረን መቀጠል አለብን ሲሉ መልዕክት አስተላልፈዋል።
እንደአድዋ ሁሉ በአንድነት ስንቆም ደማቅ ታሪክ መስራት እንደምንችል የሕዳሴው ግድብ ማሳያ ነው ያሉት ደግሞ የዳውሮ ዞን የሀገር ሽማግሌ በለጠ ባሹ ናቸው።
የዛሬው ትውልድም ዓባይን ለልማት በማዋል የራሱን ደማቅ ታሪክ ጽፏል፤ በቀጣይም እንደሀገር የተያዙ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት የልማት ትብብርን ማጠናከር ይገባናል ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅን አስመልክቶ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ መካሄዱ በወቅቱ መዘገቡ የሚታወስ ነው።