ከተማ አስተዳደሩ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል - ኢዜአ አማርኛ
ከተማ አስተዳደሩ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት የጀመራቸውን ተግባራት አጠናክሮ ይቀጥላል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ ከተማ አስተዳደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠና ጥራትና ተደራሽነትን ለማስፋት የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ እንደሚቀጥል የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች 7ሺህ 149 ተማሪዎቻቸውን በሚሊኒየም አዳራሽ አስመርቀዋል።
ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ እንደ ሀገር የተፈጠረው የይቻላል መንፈስ በተመራቂዎች ዘንድ የሚጋባና ነገን ብሩህ ለማድረግ ህልም ሰንቀው እንዲተጉ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል።
ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና በቴክኒክና ሙያ ብቁ የሆነ፣ ጠንካራ የሥራ ባህልን ያዳበረና ስነ-ምግባር ያለው ትውልድ ወሳኝ ሚና አለው ሲሉም ገልጸዋል።
ከዚህ አኳያ የዛሬው ትውልድ የትናንት ታሪክ ማውራት ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ ስንቅ የሚሆን ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ እየተጋ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው የጨበጡትን ሙያ በሥራ ዓለም ይበልጥ በማዳበር ከሀገር ፍጆታ ባለፈ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እስከማምረት ግብ ሰንቀው ሊሰሩ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ከራሳቸው ባሻገር ለሀገር ፈጣን ዕድገት መሳካት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው በማወቅ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።
ከተማ አስተዳደሩ ችግር ፈቺና ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለማፍራትና ለማበረታታት ባከናወናቸው ተግባራት አመርቂ ውጤቶች እያስመዘገበ ነው ብለዋል።
ለአብነትም በሁለቱም ዙር የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የእጅ ሥራ ውጤቶች የሆኑ ግብዓቶችን በማበርከት ለመዲናዋ ዕድገት አሻራቸውን እያኖሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ከተማ አስተዳደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋት የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው የመዲናዋ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተወዳዳሪና ተመራጭ የማሰልጠኛና የምርት ተቋም እየሆኑ ነው ብለዋል።
በተለይም በዘርፉ የሚሰጡ ስልጠናዎች የሀገሪቱን የብልፅግና አቅጣጫ የተከተሉና የገበያው ፍላጎት ላይ የተመሰረቱ እንዲሆኑ ማድረግ ችለናል ነው ያሉት።
ባለፉት ሁለት ዓመታት በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ዘርፍ ለሀገር ብልፅግና የሚጠበቅበትን ጉልህ ሚና እንዲወጣ የቴክኒክና ሙያ ዘርፉን ከወጣቶች የስራ ፈጠራ ጋር በተናበበ መልኩ በመተግበር ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።
የመዲናዋ ኮሌጆች በዓመት በአጫጭር ስልጠና ከ350ሺህ በላይ እንዲሁም ከ40ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መደበኛ የሙያ ስልጠና የመስጠት አቅም መፍጠራቸውን አንስተዋል።
አስተያየታቸውን ለኢዜአ የሰጡ ተመራቂ ተማሪዎች በበኩላቸው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ተጠናቆ በተመረቀበት ወቅት መመረቃችን ደስታችን እጥፍ ድርብ እንዲሆን አድርጎታል ብለዋል።
በስልጠናው ባገኙት ክህሎትና እውቀት የራሳቸውን ስራ ፈጥረው ህዝብንና ሀገርን ለማገልገል ዝግጁ መሆናቸውን ገልፀዋል።