ቀጥታ፡

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ታዳጊዎች በተግባር የታገዘ ስልጠና ማግኘታቸው የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያወጡ እያስቻለ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ታዳጊዎች በተግባር የታገዘ ስልጠና ማግኘታቸው የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያወጡ እያስቻለ መሆኑን የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) ገለጹ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የ2025 የሰመር ካምፕ ስልጠና የወሰዱ ታዳጊዎችን አስመርቋል።


 

በመርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።

ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) በዚሁ ወቅት እንደገለጹት፤ በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ተወዳዳሪ የሆነ የሰው ኃይል ለማፍራት በተለያየ ደረጃ ስልጠና እየተሰጠ ይገኛል።

አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ የዘመኑ ግንባር ቀደም ቴክኖሎጂ መሆኑን ጠቁመው፤ በዘርፉ ከአጫጭር እስከ ረጃጅም ስልጠናዎችን ከከፍተኛ የትምህርት ተቋማት ጋር በመሆን እየተሰጠ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

በዚህም ከሰመር ካምፕ እስከ ሦስተኛ ዲግሪ ድረስ ፕሮግራሞች ተቀርጾ ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

በ4ኛ ዙር በተካሄደው የሰመር ካምፕ ስልጠና ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የመጡ 300 ታዳጊዎች መሳተፋቸውን ተናግረዋል።

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ዘርፍ ታዳጊዎች በተግባር የታገዘ ስልጠና ማግኘታቸው የፈጠራ ክህሎታቸውን እንዲያወጡ እያስቻለ መሆኑንም ነው የተናገሩት።

በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ቤዚክስ፣ ፕሮግራሚንግ፣ ኮምፒዩተር ቪዥን፣ ሮቦቲክስ፣ ማሽን ለርኒንግ እና በተፈጥሮ ቋንቋ ቅንብር መስኮች ዙሪያ ለሁለት ወራት ስልጠና መውሰዳቸውን ገልጸዋል።

በሰመር ካምፑ ስልጠና ከወሰዱት መካከል ተማሪ ቅዱስ አላምረው በስልጠና ቆይታው ስለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ግንዛቤ ማግኘቱን ተናግሯል።


 

ተማሪ ኦብሲኔት ኡርጌሳ በበኩሏ በስልጠናው የተለያዩ ክህሎቶች ማግኘቷን ገልጻ፤ በቀጣይም የሰው ሥራ የሚያዘምንና ድካም የሚቀንስ ሮቦት ለመስራት ፍላጎት እንዳለት ገልጸለች።

የመመረቂያ ፕሮጀክት ሮቦት መስራታቸውንም ተናግራለች።

ተማሪ ቢላል ሸምሱ በበኩሉ፤ በስልጠናው ስለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ግንዛቤ መውሰዱን ገልፆ፤ በቀጣይ ትምህርቱን ሲጨርስ በኮምፒውተር ፕሮግራሚንግ ላይ ለመስራት ፍላጎት እንዳለው ተናግሯል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም