የማህበረሰቡን ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ ነው-ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር - ኢዜአ አማርኛ
የማህበረሰቡን ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ በትኩረት እየተሰራ ነው-ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር
ዱራሜ፤ መስከረም 10/2018 (ኢዜአ)፡-የማህበረሰቡን ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶች ሳይበረዙ ለትውልድ ለማስተላለፍ እየሰራ መሆኑን የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሀዲ አስታወቁ።
የከምባታ ህዝብ የዘመን መለወጫ " መሳላ" በዓል በዱራሜ ከተማ በተለያዩ ሥነ ስርዓቶች ተከብሯል፡፡
በበዓሉ ላይ የተገኙት በባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ባህልና ቋንቋ ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልመሀዲ እንዳሉት ባህላዊ እሴቶች የማህበረሰቡን አብሮት በማስተሳሰር በኩል ጉልህ ፋይዳ አላቸው።
ከእነዚህ ባህላዊ እሴቶች መካከል የከምባታ ዘመን መለወጫ የሆነው "መሳላ" ያለው የመረዳዳትና የእርቀ ሰላም እሴት እንደሚጠቀስ ገልጸዋል።
እንደ መሳላ ያሉ የመረዳዳትና የመተጋገዝ ባህላዊ እሴቶችን ሳይበረዙና ሳይከለሱ ጠብቆ ለተተኪው ትውልድ ለማሸጋገር እየተሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡
በማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፣ የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ በበኩላቸው የኢትዮጵያ የማንሰራራት ጅማሬ የሆነው ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በተመረቀበት ማግስት የተከበረው የመሰላ በዓል የተለየ ትርጉም እንዳለው ተናግረዋል፡፡
የመረዳዳትና የመተጋገዝ እሴትን ለማጠናከር የመሳላ በዓል ያለው አስተዋጽኦ ከፍተኛ ስለመሆኑ ጠቅሰው፣ የበዓሉን ትሩፋት ለሌሎች ሀገራዊ ልማቶች በማዋል የበለፀገች ሀገርን ለመገንባት እየተደረገ ያለውን ጥረት ማጠናከር ይገባል ብለዋል፡፡
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሼቱ እንደገለጹት በከምባታ በዘመን መለወጫነት የሚከበረው የመሰላ በዓል የማህበራዊ እሴትን ለማጠናከር ጉልህ ሚና ይጫወታል፡፡
በዓሉ የተጣሉ ወገኖችን በማስታረቅ፣ ያለው የሌለውን በመርዳት በአንድነት የሚከበር የፍቅር በዓል ስለመሆኑም ተናግረዋል፡፡
የበዓሉን እሴቶች አስጠብቆ ለቀጣይ ትውልድ ለማስተላለፍና በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ በርካታ ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ገልፀዋል፡፡
የመሰላ በዓል የሰላምና የአብሮነት በዓል ስለመሆኑ የተናገሩት ደግሞ የከምባታ ዞን ባህልና ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀይሉ ሀደሮ ናቸው፡፡
የሰው ልጅ ይቅርና እንሰሳት ጠግበው እንዲበሉ የተከለከለ ሣር የሚሰጥበት የመተሳሰብ በዓል መሆኑንና እሴቱን በጥናትና ምርምር በማጎልበት ለተተኪው ትውልድ ለማስተላለፍ እየተሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡