የኢትዮጵያ ዕምቅ ጥበብና ባህል በዓለም አቀፍ ደረጃ መተዋወቅ ያለበት የአፍሪካውያን የጋራ እሴት ነው - የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮጵያ ዕምቅ ጥበብና ባህል በዓለም አቀፍ ደረጃ መተዋወቅ ያለበት የአፍሪካውያን የጋራ እሴት ነው - የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ዕምቅ ጥበብና ባህል በዓለም አቀፍ ደረጃ መተዋወቅ ያለበት የአፍሪካውያን የጋራ እሴት መሆኑን የተለያዩ ሀገራት አምባሳደሮች ገለጹ፡፡
ኪን-ኢትዮጵያ "የኢትዮጵያ ማንሰራራት ብስራት" የጥበብና ባህል ጉዞ ተቀማጭነታቸውን በአዲስ አበባ ያደረጉ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች በተገኙት በኢትዮጵያ ብሔራዊ ቴአትር ባህላዊ የሙዚቃ ምሽት አዘጋጅቷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጌዲዮን ጢሞቲዎስ(ዶ/ር)፣ የትምህርት ሚኒስትር ፕሮፌሰር ብርሃኑ ነጋ፣ አምባሳደሮችና ዲፕሎማቶች ተገኝተዋል፡፡
በኢትዮጵያ የቡሩንዲ አምባሳደር ዊሊ ኒያሚትዌ ለኢዜአ በሰጡት አስተያየት፤ በኪን ኢትዮጵያ የጥበብና ባህል ምሽት ላይ በመጋበዛቸው ደስተኛ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡
በአዲስ አበባ በተለያዩ ጊዜያት የኢትዮጵያ ባህልና ኪነ ጥበብ ምሽቶችን የመታደም ልምድ እንዳላቸው በመጥቀስ፥ ለባህል ዲፕሎማሲ ትልቅ ዋጋ እሰጣለሁ ብለዋል፡፡
ኪነጥበብና ባህል የህዝብ ለህዝብ ትስስር በመፍጠር ዲፕሎማሲያዊ ትብብርን ለማጠናከር የተሻለ መንገድ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የባንግላዴሽ ወታደራዊ አታሼ ብርጋዴር ጀነራል ሻሪፉል ኢስላም የኢትዮጵያ የቋንቋና ባህል ብዝሃነት አስደናቂ መሆኑን ተመልክቻለሁ ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ እውነትም ምድረ ቀደምትና የረጅም ዘመን ታሪክ ባለቤት መሆኗን በመርሃ ግብሩ ላይ በቀረበው የኪነጥበብና የባህል ትዕይንት መገንዘባቸውንም ገልጸዋል፡፡
ትዕይንቱ የሀገሪቱን የተለያዩ አካባቢዎች ባህልና የጥበብ ሀብት እንዲያውቁ እንዳስቻላቸው በመግለፅ፤ ኢትዮጵያ ውጤታማ የባህል ዲፕሎማሲ እያከናወነች መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በኢትዮጵያ የናይጀሪያ ምክትል አምባሳደር ማክሲ ኦክቤዴ የኪነ ጥበብና ባህል ምሽቱ አስደናቂ እንደነበር አንስተዋል፡፡
ኢትዮጵያ በባህልና ኪነ ጥበብ የበለጸገች፣ አፍሪካዊ ትስስርን የሚያጠናክር አህጉሪቱን ከፍ አድርጎ የሚያስጠራ እምቅ እሴት እንዳላት አሳይታለች ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ባዘጋጀችው የጥበብ መድረክ አፍሪካን የሚወክል ሥራ ነው የቀረበው ያሉት አምባሳደር ማክሲ፥ ይህም በዓለም አቀፍ ደረጃ በአግባቡ መተዋወቅ እንዳለበት ጠቅሰዋል፡፡