በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት ስኬታማነት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል - ኢዜአ አማርኛ
በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት ስኬታማነት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ ተገብቷል
ወላይታ ሶዶ፤ መስከረም 10/2018 (ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት ስኬታማነት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን የክልሉ ፖሊስ አስታወቀ።
በክልሉ በቀጣይ የጊፋታ፣ የጋሞ ዮ ማስቃላ፣ የጎፋ ገዜ ማስቃላ እና በሌሎችም የአደባባይ በዓላት በተከታታይ የሚከበሩ ይሆናል።
እነዚህ በአላት ሲከበሩ በተረጋጋና በተሳካ መልኩ እንዲከበሩ የተደረገውን ዝግጅት በማስመልከት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን የወንጀል መከላከልና የትራፊክ አደጋ መከላከል ዘርፍ ኃላፊ ምክትል ኮሚሽነር ደግፌ ደበላ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫቸውም በክልሉ በአደባባይ ለሚከበሩ በዓላት ሰላማዊ ክንውን ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ስራ መግባቱን አንስተው በተለይም ፖሊስ በጸጥታ ማስከበር ረገድ በሁሉም መልኩ የተሟላ እና የተቀናጀ ስምሪት ማድረጉን ተናግረዋል።
የፖሊስ ስምሪት የትራፊክ እንቅስቃሴን ከማሳለጥ ጀምሮ በዓላቱ በሚከበሩባቸው አካባቢዎች የጸጥታ ቁጥጥርና ጥበቃ ስራዎች በተጠናከረ መልኩ የሚከናወኑ መሆኑን አንስተዋል።
በክልሉ በቀጣይ የጊፋታ፣ የጋሞ ዮ ማስቃላ፣ የጎፋ ገዜ ማስቃላ እና በሌሎችም የአደባባይ በዓላት በተከታታይ የሚከበሩ መሆኑን አንስተው ለዚህም ፖሊስ ከሌሎች የጸጥታና የሚመለከታቸው አካላት ጋር የተቀናጀና የተሟላ ዝግጅት መደረጉን ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።
በሁሉም አካባቢዎች በአላቱ ሲከበሩ ህብረተሰቡ በተለይም የሀሰተኛ ብር ኖቶችና በዓድ ነገሮችን ቀላቅለው ከሚሸጡ ሰዎች ጥንቃቄ ማድረግ እንዳለበትም አስገንዝበዋል።
እነዚህና መሰል የወንጀል ጥርጣሬዎች ሲያጋጥሙ በአቅራቢያ ለሚገኝ ፖሊስ ፈጥኖ ጥቆማ መስጠት እንደሚገባም ተናግረዋል።