ቀጥታ፡

መንግሥት በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር ትኩረት ሰጥቷል - ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር መንግስት በትኩረት እየሰራ መሆኑን ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ ገለጹ።

የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት የ2025 የሰመር ካምፕ ስልጠና የወሰዱ ታዳጊዎችን አስመርቋል።

በመርሃ ግብሩ ላይ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ተመስገን ጥሩነህ፣ የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ወርቁ ጋቸና(ዶ/ር) እና ሌሎች የመንግስት ከፍተኛ ስራ ኃላፊዎች ተገኝተዋል።


 

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚሁ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፥ በቴክኖሎጂ ዘርፍ ብቁና ተወዳዳሪ ትውልድ ለመፍጠር መንግስት በትኩረት እየሰራ ይገኛል ብለዋል።

የነገ ሀገር ተረካቢ ወጣቶችና ታዳጊዎች ዘመኑን የዋጀ የቴክኖሎጂ እውቀት እንዲያዳብሩ ካለፉት ሦስት ዓመታት ወዲህ በክረምት መርሃ ግብር የሰው ሠራሽ አስተውሎት ስልጠና እየተሰጠ መሆኑን ተናግረዋል።

የመጪው ዘመን አብዮት በሆነው በሰው ሰራሽ አስተውሎት ላይ ተወዳዳሪ መሆን የሚያስችሉ ስራዎች እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ያነሱት።


 

ከዚህ አኳያ መንግስት የኢትዮጵያ አርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ኢንስቲትዩትን በማደራጀት በዘርፉ ጠንካራ ሀገራዊ አቅም እየፈጠረ ነው ብለዋል።

ዲጂታል ኢትዮጵያን እውን ለማድረግ በሰው ሰራሽ አስተውሎት እና በሌሎች የቴክኖሎጂ ፈጠራዎች ላይ አበረታች ተግባራት እየተከናወኑ እንደሚገኙም ነው ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያነሱት።

በተለይ ወጣቶችን በማሰልጠን በዘርፉ ክህሎት እና እውቀት እንዲያዳብሩ የተጀመሩ ሥራዎች ተጠናክረው እንደሚቀጥሉም አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም