የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት ሌሎች የአፍረካ ሀገራት ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ ነው - አፍሪካውያን ጋዜጠኞች - ኢዜአ አማርኛ
የአዲስ አበባ ፈጣን ዕድገት ሌሎች የአፍረካ ሀገራት ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ ነው - አፍሪካውያን ጋዜጠኞች
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ አዲስ አበባ ያስመዘገበችው ፈጣን ለውጥና ዕድገት ሌሎች የአፍረካ ሀገራት ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ መሆኑን አፍሪካውያን ጋዜጠኞች ገለጹ።
ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት የመጡ የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎች በአዲስ አበባ ከተማ ጉብኝት አድርገዋል።
ባለሙያዎቹ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ሙዚየምን እና የአዲስ አበባ ዋና ዋና ጎዳናዎችን የምሽት ድባብ ተዘዋውረው ጎብኝተዋል።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፌሰር አበባው አያሌው በሙዚየሙ ስለሚገኙ ቅርሶች እና አጠቃላይ የሙዚየም እንቅስቃሴን በተመለከተ ለጋዜጠኞቹ ገለጻ አድርገውላቸዋል።
ከኬንያ የመጣው ጋዜጠኛ ጃክሰን ኦካታ አዲስ አበባን ለመጀመሪያ ጊዜ ማየቱን ጠቅሶ፥ ከተማዋ ከዚህ ቀደም በሩቅ ከሚያውቀው የላቀ ውብ ሆና ማግኘቱን ተናግሯል።
በተጨማሪም መንገዶችን ከአረንጓዴ ልማት ጋር ለማስተሳሰር የተከናወኑ ስራዎች የሚደነቁ መሆናቸውን በማንሳት፥ ይህም ሁሉም የአፍሪካ ከተሞች ሊከተሉት የሚገባ ተምሳሌታዊ ተግባር ነው ብሏል።
ከማላዊ የመጣችው ጋዜጠኛ ካትሪን ቴምቦ በአዲስ አበባ ያላትን ቆይታ እንደወደደችው እና ጥሩ ጊዜን እያሳለፈች መሆኑን ገልጻለች።
ከተማዋ ውብ መሆኗን እና በከተማዋ ያለው ለውጥ አስደናቂ መሆኑንም አንስታለች።
ኬንያዊቷ ጋዜጠኛ አጋታን ጎዞ በበኩሏ ከዚህ ቀደም ከተማዋን የመጎብኘት ዕድል ማግኘቷን አስታውሳ አሁን ላይ በከተማዋ ብዙ ለውጥ ማየቷን መስክራለች።
የተለያዩ ቦታዎችን ተዘዋውራ መመልከቷን ገልጻ ከፍተኛ የአካባቢ ጥበቃና የአረንጓዴ ልማት መኖሩንና የህብረተሰቡ ተሳትፎም የላቀ መሆኑን መገንዘቧን ነው የጠቀሰችው።
ሩዋንዳዊው ጋዜጠኛ ሚሼል ኩዚዛም የአዲስ አበባን እድገት እንዲሁም የከተማዋን ለውጥ ሁሉም ሊጎበኘው የሚገባው ነው ብሏል።
የኢትዮጵያ በተለይም የአዲስ አበባ የለውጥ ጎዳና ለአፍሪካውያን ምሳሌ የሚሆንና በጋራ ትጋት አህጉሪቱን ማሳደግ እንደሚቻል ያሳየ መሆኑንም አመላክቷል።
አዲስ አበባ ድንቅ ከተማ መሆኗን የገለጸው ደግሞ ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ አዲስ አበባ የመጣው ኬንያዊው ጋዜጠኛ ጆን ሪኦጋ ነው።
በከተማዋ ያለው የትራፊክ ፍሰት፣ የመንገዶች ስፋት እንዲሁም ለእግረኞች በቂ ቦታ መዘጋጀቱ እንዳስደነቀው ተናግሯል።