ኢትዮጵያ መድን የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ጨዋታውን ከዛንዚባሩ ምላንዴጌ ጋር ዛሬ ያካሂዳል - ኢዜአ አማርኛ
ኢትዮጵያ መድን የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ማጣሪያ ጨዋታውን ከዛንዚባሩ ምላንዴጌ ጋር ዛሬ ያካሂዳል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ ኢትዮጵያ መድን የ2025/26 የካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ከዛንዚባሩ ምላንዴጌ ጋር ዛሬ ያደርጋል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
ኢትዮጵያ መድን በካፍ ሻምፒዮንስ ሊግ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚወዳደረው የ2017 ዓ.ም የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አሸናፊ በመሆኑ ነው።
በገብረመድህን ኃይሌ የሚሰለጥነው ቡድን በውድድሩ ላይ ሲሳተፍ በታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ተጋጣሚው ምላንዴጌ ኤፍሲ በሻምፒዮንስ ሊጉ ማጣሪያ የሚሳተፈው የዛንዚባር ፕሪሚየር ሊግ የወቅቱ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ሲሆን የሊጉን ዋንጫ ሰባት ጊዜ አንስቷል።
ምላንዴጌ እ.አ.አ በ2020/21 በሻምፒዮንስ ሊጉ የመጀመሪያ ዙር ማጣሪያ ተሳትፎ አድርጎ በቱኒዚያው ሴፋክሲያን ሽንፈት አስተናግዶ ከውድድሩ መሰናበቱ የሚታወስ ነው።
ኢትዮጵያ መድን እና ምላንዴጌ ኤፍሲ የመልስ ጨዋታቸውን መስከረም 17 ቀን 2018 ዛንዚባር ላይ ያደርጋሉ።
መድን በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በመጨረሻው ዙር ከሩዋንዳው ኤፒአር እና ከግብጹ ኤፍሲ ፒራሚድስ አሸናፊ ጋር ይጫወታል።