በጅማ ዞን የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል - ኢዜአ አማርኛ
በጅማ ዞን የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር ወንጀልን አስቀድሞ ለመከላከል ምቹ ሁኔታ ተፈጥሯል
ጅማ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን የማሕበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በማጠናከር የወንጀል ድርጊትን አስቀድሞ በቅንጅት ለመከላከል ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን የዞኑ ፖሊስ መምሪያ አስታወቀ።
የዞኑ ፖሊስ መምሪያ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ሀላፊ ዋና ኢንስፔክተር አዲሱ ሀይሉ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የህግ የበላይነትን ለማስከበር የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስን የማደራጀት ስራ ሲከናወን ቆይቷል።
በሁሉም ወረዳዎች ለዚሁ ተግባር የሚውሉ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶች ህዝቡን በማስተባበር መገንባታቸውን አንስተዋል።
በማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት ጽህፈት ቤቶችም ሙያዊ ስልጠና የወሰዱ አባላት በየቀበሌው ተመድበው ስራቸውን እያከናወኑ መሆኑን አስረድተዋል።
ባለፈው አመት ብቻ በዞኑ 40 የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ ጽህፈት ቤቶች በህብረተሰብ ተሳትፎ ተገንብተው ወደ ስራ መግባታቸውን ለአብነት ጠቅሰዋል።
በዚህም በየአካባቢው የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎትን በማስፋፋት የወንጀል ድርጊትን ቀድሞ በመከላከል የህግ የበላይነትን ለማሰከበር በቅንጅት በመሰራቱ ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።
የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት በመስፋፋቱ በተለይም ህብረተሰቡ ከፖሊስ ጋር በመቀናጀት አካባቢውን በአግባቡ እንዲጠብቅ ማስቻሉን ተናግረዋል።
በአገልግሎቱም ህብረተሰቡ የወንጀል ድርጊትን ሲመለከት ፍጥኖ መረጃ እንዲሰጥ እድል የተፈጠረ ሲሆን፤ ሰላምና ጸጥታ ጉዳይ ተከታታይ ውይይቶችም ይደረጋሉ ብለዋል።
በአጠቃላይ የማህበረሰብ አቀፍ ፖሊስ አገልግሎት የህብረተሰቡን ተሳትፎ ባሳደገ መልኩ ህግ እንዲከበር ማስቻሉን ተናግረዋል።