ቀጥታ፡

የሕዳሴ ግድብ በራሳቸው አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን ለመገንባት የሚፈልጉ የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚወስዱበት ፕሮጀክት ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018 (ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ በራሳቸው አቅም ግዙፍ ፕሮጀክቶችን መገንባት የሚፈልጉ የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት ሊወስዱበት የሚገባ ፕሮጀክት መሆኑን አሜሪካዊው የፖለቲካ ተንታኝ አንድሪው ኮሪብኮ(ዶ/ር) ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ጳጉሜን 4 ቀን 2017 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) መመረቁ የሚታወስ ነው።

በምረቃ ስነ ስርዓቱ ላይ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች ተገኝተዋል።

የመሪዎቹ መገኘት የቀጣናው ሀገራት በጋራ የመልማት መሻት እንዲሁም አፍሪካ በራሷ የማድረግ አቅም እንዳላት በግልጽ ያመላከተ ነው።

አንድሪው ኮርቦ ከኢዜአ ጋር በነበራቸው ቆይታ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በደቡብ ንፍቀ ዓለም የሚገኙ ሀገራት የራሳቸውን አቅም በመገንባት ሉዓላዊነታቸውን የማጠናከር የብዝሃ ወገን የትብብር ማዕቀፍ ነጸብራቅ ነው ብለዋል።


 

ኢትዮጵያ በአፍሪካ ውስጥ የመሪነት ሚናዋን እያጠናከረች ነው፣ ቅኝ አለመገዛቷና የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ መሆኗ በአህጉሪቱ ታሪክ ውስጥ ያላትን ሚና ያሳያልም ነው ያሉት።

ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያ በኢነርጂ ራሷን የመቻል ጉዞዋን የሚያሳካ መሆኑን ገልጸው በርካታ ዜጎች የኤሌክትሪክ ኃይል ተጠቃሚ በማድረግ እምቅ የኢኮኖሚ አቅምን ለመጠቀም ምቹ አጋጣሚ መፍጠሩን አመልክተዋል።

ኢትዮጵያ የቀጣናው መሪ ሀገር ናት ያሉት ተንታኙ ሁሉም ጎረቤቶቿ በትብብር በመስራት ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ እንደሚችሉ ማሳያ መሆኗንም ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ የሕዳሴ ግድብን ከሀሳብ መጠንሰሱ አንስቶ በራሷ ፋይናንስ ገንብታ ወደ ስራ ማስገባቷ ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶችን በራሳቸው አቅም ለመገንባት ለሚፈልጉ የአፍሪካ ሀገራት ትልቅ ትምህርት የሚሰጥ መሆኑን ነው የገለጹት።

ሕዳሴ ግድብ የአፍሪካን አቅም የበለጠ የሚገነባና የዚህ ዘመን የብዝሃ ዓለም የፖለቲካ ስርዓት እያደገ መምጣቱን የሚያሳይ ነው ብለዋል።


 

ከቀጣናዊ አንድምታ አኳያ ግድቡ ኢትዮጵያ በአባይ ወንዝ በመጠቀም ብሄራዊ ፍላጎቶቿን የማስጠበቅ አቅም እንዳላት ማሳየቷን ገልጸው የታችኛው ተፋሰስ ሀገራት ከኢትዮጵያ ጋር የትብብር አማራጭን መከተል እንደሚገባቸው አስገንዝበዋል።

ኢትዮጵያ ለጎረቤት ሀገራት የምትሸጠው የኤሌክትሪክ ኃይል ቀጣናዊ ትብብርን እንደሚያጠናክርም ነው ተንታኙ የገለጹት።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የቀጣናው ሰላም እና ልማት አቀጣጣይ ሞተር ነው ሲሉም ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም