ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የማንሰራራት ከፍታ መሸጋገሪያችን ነው - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የማንሰራራት ከፍታ መሸጋገሪያችን ነው - ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር)
ሆሳዕና፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ):- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በስኬት መጠናቀቅ ለጀመርነው የማንሰራራት ከፍታ መሸጋገሪያ ማማችን ነው ሲሉ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) ገለጹ።
"በሕብረት ችለናል" በሚል መሪ ሃሳብ የግድቡ በስኬት መጠናቀቅን በማስመልከት በክልል ደረጃ ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ዛሬ በሆሳዕና ከተማ ተካሂዷል።
ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው(ዶ/ር) በወቅቱ እንደገለጹት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ኢትዮጵያውያን በጋራ ያሳኩት አኩሪ ፕሮጀክት ነው።
ኢትዮጵያውያን በሕብረት፥ በይቻላልና በፅናት ለስኬት ያበቁት የዚህ ትውልድ ጥንካሬ ማሳያ ነው ብለዋል።
በተለይም የለውጡ መንግስት የግድቡ ግንባታ ከነበሩበት ውስብስብ ችግሮች በማውጣት ለውጤት አብቅቶታል ሲሉም ገልጸዋል።
ግድቡ የጋራ ብልፅግና ማምጣት የሚያስችል ፕሮጀክትና ለጀመርነው የማንሰራራት ከፍታ መሸጋገሪያ ማማችን ነው ብለዋል።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ስኬት በቀጣይ ለሚከናወኑ ትላልቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች መሠረት የጣለና ኢትዮጵያ በሀብቷ የመጠቀም መብቷን በተግባር ያረጋገጠችበት መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ ሕዝብም ለሕዳሴ ግድብ ግንባታ የሚጠበቅበትን ሁሉ ማድረጉን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሕዝቡ ላደረገው ድጋፍም ምስጋና አቅርበዋል።
በሰልፉ ላይ የክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።