ቀጥታ፡

የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ምሩቃን በመዲናዋ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች አሻራቸውን እያሳረፉ ይገኛሉ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 10/2018(ኢዜአ)፦ የቴክኒክና ሙያ ተቋማትና ምሩቃን የእጅ ሥራ ውጤቶቻቸውን ለመዲናዋ የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች በግብዓትነት በማቅረብ ለከተማዋ ዕድገት አሻራቸውን እያኖሩ እንደሚገኙ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።

የአዲስ አበባ ከተማ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኮሌጆች 7ሺህ 149 ተማሪዎቻቸውን በሚሊኒየም አዳራሽ አስመርቀዋል።

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ በምረቃ ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው የእንኳን ደስ አላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


 

በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መመረቅ እንደ ሀገር የተፈጠረው የይቻላል መንፈስ በተመራቂዎች ዘንድ የሚጋባና ነገን ብሩህ ለማድረግ ህልም ሰንቀው እንዲተጉ መነሳሳትን የሚፈጥር መሆኑንም ተናግረዋል።

ለሀገር ዕድገትና ብልፅግና በቴክኒክና ሙያ ብቁ የሆነ፣ ጠንካራ የሥራ ባህልን ያዳበረና ስነ-ምግባር ያለው ትውልድ ወሳኝ ሚና አለው ብለዋል።

ከዚህ አኳያ የዛሬው ትውልድ የትናንት ታሪክ ማውራት ብቻ ሳይሆን ለነገው ትውልድ ስንቅ የሚሆን ታሪክ ሰርቶ ለማለፍ እየተጋ እንደሚገኝ ገልጸዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ችግር ፈቺ የሆኑ ሥራ ፈጣሪ ወጣቶችን ለማፍራትና ለማበረታታት በጀት መድቦ ባከናወናቸው ተግባራት አመርቂ ውጤቶችን እያስመዘገበ ነው ብለዋል።


 

ለአብነትም በሁለቱም ዙር የኮሪደርና ሌሎች የልማት ሥራዎች የቴክኒክና ሙያ ተቋማት የእጅ ሥራ ውጤቶች የሆኑ ግብዓቶችን በማበርከት ለመዲናዋ ዕድገት አሻራቸውን እያኖሩ ይገኛሉ ነው ያሉት።

ተመራቂዎች በስልጠና ቆይታቸው የጨበጡትን ሙያ በሥራ ዓለም ይበልጥ በማዳበር ከሀገር ፍጆታ ባለፈ ለዓለም ገበያ የሚቀርቡ ምርቶችን እስከማምረት ግብ ሰንቀው ሊሰሩ እንደሚገባ አስረድተዋል።

ከራሳቸው ባሻገር ለሀገር ፈጣን ዕድገት መሳካት ትልቅ ኃላፊነት እንዳለባቸው በማወቅ በሙሉ አቅማቸው እንዲሰሩም ከንቲባዋ ጥሪ አቅርበዋል።

ከተማ አስተዳደሩ ከመቼውም ጊዜ በላይ የቴክኒክና ሙያ ስልጠናን ጥራትና ተደራሽነት ለማስፋት የጀመራቸውን ተግባራት ይበልጥ አጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።


 

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ የሥራና ክህሎት ቢሮ ኃላፊ ጥራቱ በየነ በበኩላቸው የመዲናዋ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጆች ተወዳዳሪና ተመራጭ የማሰልጠኛና የምርት ተቋም እየሆኑ ነው ብለዋል።

የቴክኒክና ሙያ ዘርፍን ከወጣቶች የስራ ፈጠራ ጋር በተናበበ መልኩ በመተግበርም ተጨባጭ ውጤት እየተመዘገበ መሆኑን ተናግረዋል።

የመዲናዋ ኮሌጆች በዓመት በአጫጭር ስልጠና ከ350ሺህ በላይ እንዲሁም ከ40ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች መደበኛ የሙያ ስልጠና የመስጠት አቅም መፍጠራቸውን አንስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም