ቀጥታ፡

የጣና ሐይቅ ገዳማትና አዋሳኝ ውኃ አዘል መልከዓ-ምድርን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፡- የጣና ሐይቅ ደሴተ ገዳማትና አዋሳኝ ውኃ አዘል መልከዓ-ምድር የባህልና የተፈጥሮ መካነ-ቅርስ በተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ።

የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን የቅርስ አሥተዳደር ዘርፍ መሪ ሥራ አስፈጻሚ ፀሐይ እሸቴ ለኢዜአ እንዳሉት፤ ቅርሱ በፈረንጆቹ ሐምሌ 2026 ዓ.ም በኮሪያ ሪፐብሊክ ቡሳን ከተማ በሚካሄደው የዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ኮሚቴ 48ኛ መደበኛ ጉባዔ ላይ እንደሚመዘገብ ይጠበቃል።

ለቅርሱ ምዝገባ አስፈላጊ ቅድመ ሁኔታዎች አካል የሆነው የምዝገባ ሠነድ ቀደም ሲል ለዩኔስኮ ተልኮ ተቀባይነት ማግኘቱንም አስታውሰዋል።

እንዲመዘገብ ከተጠየቀው ቅርስ ጋር በተያያዘ ሠነዱ ለጉባዔው ከመቅረቡ በፊት መከናወን ያለባቸው አስገዳጅ የቅድመ ዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑንም አስረድተዋል።


 

በቀረበው የምዝገባ ሠነድ መሠረት የቅርሱን ይዘት እና ቅርሱ የሚገኝበትን ሁኔታ ለመገምገም በቅርቡ የዩኔስኮ ልዑክ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚመጣም ጠቁመዋል።

የልዑካን ቡድኑ አባላት ከዓለም አቀፍ የመታሰቢያ ሐውልቶች እና ስፍራዎች ምክር ቤት እና ከዓለም አቀፍ የተፈጥሮ ቅርስ ጥበቃ ኅብረት የተውጣጡ ከፍተኛ የዘርፉ ምሁራን መሆናቸውን አመላክተዋል።

እስካሁን ኢትዮጵያ 12 የሚዳሰሱ ቅርሶችን በዓለም አቀፍ ቅርስነት ማስመዝገቧንም አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም