ቀጥታ፡

ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ይካሄዳሉ 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፦ በጃፓን ቶኪዮ እየተካሄደ የሚገኘው 20ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ኢትዮጵያውያን አትሌቶች የሚሳተፉባቸው ሁለት የፍጻሜ ውድድሮች ዛሬ ከእኩለ ሌሊት በኋላ ይደረጋሉ።

ከሌሊቱ 7 ሰዓት ከ30 በሴቶች የ20 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር አትሌት ስንታየሁ ማስሬ ትወዳደራለች።

አትሌት ስንታየሁ በውድድሩ ላይ እንድትሳተፍ የተመረጠችው እ.አ.አ በ2024 በካሜሮን ዱዋላ በተካሄደው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያ ማግኘቷን ተከትሎ ነው።

ስንታየሁ በካሜሮኑ ውድድር 1 ሰዓት ከ37 ደቂቃ ከ46 ሴኮንድ አንደኛ በመውጣት በርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቷን ማስመዝገቧ የሚታወስ ነው።

አትሌቷ እ.አ.አ በ2023 በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች በ20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ተወዳድራ የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።

እ.አ.አ በ2011 በኮትዲቭዋር አቢጃን በተደረገው ራተኛው ከ18 እና 20 ዓመት በታች የአፍሪካ ታዳጊዎች አትሌቲክስ ሻምፒዮና የ10 ኪሎ ሜትር የርምጃ ውድድር ሶስተኛ በመውጣት የነሐስ ሜዳሊያ ማግኘቷ የሚታወስ ነው።

በተጨማሪም ስንታየሁ እ.አ.አ በ2018 በአልጄሪያ በተካሄደው ሶስተኛ የአፍሪካ ወጣቶች ጨዋታ በአምስት ኪሎ ሜትር ርምጃ ውድድር የብር ሜዳሊያ አግኝታለች።


 

ከሌሊቱ 9 ሰዓት ከ55 በሚደረገው የወንዶች የ20 ኪሎ ሜትር ርምጃ ፍጻሜ አትሌት ምስጋና ዋቁማ ኢትዮጵያን ወክሎ ይወዳደራል።

አትሌት ምስጋና በውድድሩ ላይ እንዲሳተፍ የተመረጠው በ20 ኪሎ ሜትር የወንዶች ርምጃ ዓለም አቀፍ የደረጃ ሰንጠረዥ 14ኛ ላይ በመገኘቱ ባገኘው የተሳትፎ ኮታ ነው።

ምስጋና እ.አ.አ በ2024 በፓሪስ በተካሄደው 33ኛው የኦሊምፒክ ጨዋታዎች በ20 ኪሎ ሜትር የወንዶች ርምጃ ውድድር ስድስተኛ መውጣቱ ይታወሳል።

በወቅቱ 1 ሰዓት ከ19 ደቂቃ ከ31 ሴኮንድ የገባበት ጊዜ የርቀቱ የግል ምርጥ ሰዓቱ ነው።  

አትሌቱ እ.አ.አ በተርኪዬ አንታሊያ በተካሄደው የዓለም የርምጃ ውድድር ሻምፒዮና 1 ሰዓት ከ20 ደቂቃ ከ51 ሴኮንድ 10ኛ ወጥቷል። 

እ.አ.አ በ2023 በጋና በተካሄደው 13ኛው የአፍሪካ ጨዋታዎች እና እ.አ.አ በ2024 በካሜሮን ዱዋላ በተካሄደው 23ኛው የአፍሪካ አትሌቲክስ ሻምፒዮና በርቀቱ የወርቅ ሜዳሊያዎችን አግኝቷል።

በርምጃ ውድድሮች ስንታየሁ ማስሬ እና ምስጋና ዋቁማ ጠንካራ ተፎካካሪ እንደሚሆኑ ይጠበቃል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም