ቀጥታ፡

በጠንካራ አንድነት ያሳካነውን ግዙፍ ፕሮጀክት በሌሎች ዘርፎች ላይም ለመድገም ቁርጠኞች ነን-የህዝባዊ ሰልፍ ታዳሚዎች

ቦንጋ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ) :- በጠንካራ አንድነት ያሳካነውን ታላቁን የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሌሎች የልማት ዘርፎች ለመድገም ቁርጠኛ ነን ሲሉ በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ቦንጋ ከተማ የህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ ታዳሚዎች ገለፁ።

የህዳሴ ግድብ መጠናቀቅን አስመልክቶ ክልል አቀፍ ህዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በቦንጋ ከተማ ተካሄዷል።

የሰልፉ ታዳሚዎች ፤ በጠንካራ አንድነት ያሳካነውን ታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ በሌሎች የልማት ዘርፎች ለመድገም ቁርጠኛ ነን ሲሉ ገልጸዋል።


 

በክልሉ ከቤንች ሸኮ ዞን የመጡት አቶ ወልደየስ ዘለቀ እና ከሸካ ዞን የመጡት ኢንስፔክተር ደመረ አገሎ የህዳሴው ግድብ መጠናቀቅ አንድ ከሆንን የማንወጣው ነገር እንደሌለ ማሳያ ነው ብለዋል።


 

የትውልዱ ኩራትና ዳግማዊ አድዋ የሆነውን የህዳሴ ግድብ ግንባታን ለማጠናቀቅ ያሳየነውን ድጋፍና ህብረት በሌሎች ግዙፍ ሀገራዊ የልማት ስራዎች ላይ ለመድገም ቁርጠኛ ነን ብለዋል።

ዳግማዊ አድዋ በዘመናችን ተፈፅሞ በማየታችን ትልቅ ደስታ ተሰምቶናል ያሉት የቦንጋ ከተማ ነዋሪዋ ወይዘሮ ሀና ወልደማሪያም እና ከኮንታ ዞን የመጡት ሻምበል ጀበሌ ዱላ ናቸው።


 

በቀጣይም ኢትዮጵያ የሰነቀችው ራዕይ ተሳክቶ ለማየት እንደሀገር የተያዙ ዕቅዶችን ለማሳካት የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በህዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ "የህዳሴው ግድብ የህብረታችን አርማ የብልፅግናችን አሻራ ነው" ብለዋል። 


 

በጋራ መቆማችን ውስብስብ ችግሮችን ተሻግረን ትልልቅ የልማት ውጥኖችን ማሳካት እንደሚቻል ያረጋገጠ ነው ያሉት  ኢ/ር ነጋሽ ዋጌሾ (ዶ/ር) ከተባበርንና በጋራ ከቆምን ከከፍታ ጉዟችን የሚያስቆመን ኃይል የለም ሲሉም ተናግረዋል። 

ግድቡ በላባችን፣ በደማችንና በገንዘባችን ያፀናነው ሕያው የምህንድስና ጥበብና የማህበረሰብ የወል ቅርስ ነው በማለት ይህን ግዙፍ ፕሮጀክት በማጠናቀቅ ያሳየነውን ስኬት በሌሎች ላይም እንደግማለን ሲሉ አረጋግጠዋል።

በቦንጋ ከተማ በተካሄደው ክልል አቀፍ የደስታ መግለጫ ሰልፍ ላይ የክልል ከፍተኛ አመራሮች፣ ከሁሉም ዞኖች የተወጣጡ የህብረተሰብ ተወካዮችና የቦንጋ ከተማ ነዋሪዎች ተሳትፈዋል። 

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም