በሲዳማ ክልል ሀብትን በአግባቡ በማስተዳደር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው - ኢዜአ አማርኛ
በሲዳማ ክልል ሀብትን በአግባቡ በማስተዳደር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ ነው

ሀዋሳ ፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦በሲዳማ ክልል ሀብትን በአግባቡ በማስተዳደር የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሀም ማርሻሎ ተናገሩ ፡፡
የሲዳማ ክልል ገንዘብ ቢሮ የሴክተር ጉባኤ በሀዋሳ ከተማ ተካሂዷል ፡፡
በጉባኤው ላይ የተገኙት የክልሉ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ አብርሀም ማርሻሎ፤ በክልሉ ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብና በማስተዳደር ህዝቡን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤት እያመጡ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በተለይ በ2017 በጀት ዓመት ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የክልሉን አብዛኛውን ወጪ በውስጥ አቅም ለመሸፈን በተሰራው ሥራ ከ50 በመቶ በላይ የሚሆነውን ወጪ መሸፈን እንደተቻለ አስረድተዋል፡፡
የተሰበሰበውን ሀብት በቀጥታ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ በሚያደርጉ ተግባራት ላይ ለማዋልም በርካታ ሥራዎች መሰራታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም የንፁህ መጠጥ ውሃ፣ የመስኖ፣ የመንገድ፣ የጤና፣ የትምህርትና ሌሎች መሠረተ ልማት ግንባታዎችን በማከናወን ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
ለእነዚህ ሥራዎች የተመደበው ሀብት ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥም የተጠናከረ የኦዲት ሥርዐት በመዘርጋት ውጤታማ ሥራ መስራት ተችሏልም ብለዋል ፡፡
በ2017 በጀት ዓመት በአጠቃላይ ኦዲት ከተፈተሹ 17 የክልል ተቋማት ውስጥ አሥሩ ጤናማ የፋይናንስ ሥርዐት እንዳላቸው መረጋገጡን ጠቅሰው በሰባቱ ደግሞ የታዩ ጥቃቅን ጉድለቶች እንዲታረሙ መደረጉን አብራርተዋል ፡፡
የዲጂታል አገልግሎት አሰጣጥን በመዘርጋት የተቀላጠፈ ማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎት በመስጠት ገቢ አሰባሰብን ለመለወጥ በትኩረት እንደሚሰራም አመልክተዋል፡፡
የክልሉ ገንዘብ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሌ ሀርሲሳ በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የፋይናንስ ሥርዐት ክፍተቶችን ለመሙላት የሚያስችሉ የአሰራር ሥርዐትና የሕግ ማዕቀፎች ማሻሻያ ሲደረግ መቆየቱን አውስተዋል፡፡
በ2018 የኢሌክትሮኒክ የመንግስት ግዢ እና የኤሌክትሮኒክ ክፍያ ሥርዐትን ለማጠናከር በልዩ ትኩረት እንደሚሰራ ገልጸዋል።
በጉባኤው ላይ የክልል ፣ የዞን እንዲሁም የከተማ አስተዳደርና የወረዳ አመራሮችና ባለሙያዎች ተገኝተዋል ፡፡