ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ በመቀሌ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አስጀመሩ - ኢዜአ አማርኛ
ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ በመቀሌ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ አስጀመሩ

መቀሌ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፡- የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በመቀሌ ከተማ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ አኖሩ።
ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ የበጎ ፈቃድ አገልግሎቶች እየተለመዱና እየተስፋፉ ሲሆን፤ በተለይም የአቅመ ደካማ ወገኖች እና አረጋውያንን ቤቶች በማደስና በመገንባት ጭምር በርካታ ተቋማትና ግለሰቦች እየተሳተፉ ይገኛሉ።
በአዲስ አበባ እና በክልል ከተሞች ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች ጭምር የሚሳተፉበት የቤት ግንባታና እድሳት ተግባር እየተከናወነ ነው።
በዚህም መሰረት የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር እና የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር በመቀሌ ለአቅመ ደካማ ወገኖች የመኖሪያ ቤቶች ግንባታ ማስጀመሪያ የመሰረት ድንጋይ አኑረዋል።
የግንባታውን የመሰረት ድንጋይም የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብረቢ ሁለቱንም ተቋማት በመወከል አስቀምጠዋል።
በዚሁ መርሃ ግብር ላይ ሚኒስትሯ ባደረጉት ንግግር፤ የመኖሪያ ቤቶቹ በጥራትና በፍጥነት ተጠናቀው ለነዋሪዎች ይተላለፋል ብለዋል።
በመኖሪያ ቤት ግንባታውም ይሁን በሌሎች በጎ ተግባራት ዜጎችን ተጠቃሚ ለማድረግ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ እየሰራ መሆኑን ገልጸው በሁሉም አካባቢዎች ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል።
ከዚሁ መርሃ ግብር በተጓዳኝም ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶቹ ለተማሪዎች የትምህርት ቁሳቁስ ድጋፍ አድርገዋል።