ቀጥታ፡

ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ከመከላከል ጎን ለጎን ደህንነቱ የተረጋገጠ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ሊጠናከር ይገባል

አዳማ፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ከመታገል ጎን ለጎን ቀላል፣ መደበኛና ደህንነቱ የተረጋገጠ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪት ሊጠናከር  እንደሚገባ የፍትህ ሚኒስቴር አስገነዘበ።

ሚኒስቴሩ በዓለም አቀፍ የፍልሰት ድርጅት እና በዓለም አቀፍ የህጻናት አድን ድርጅት ድጋፍ የትብብር ጥምረቶች የ2017 የሥራ አፈጻጸም ግምገማና የቀጣይ አቅጣጫ ላይ ከባለድርሻ አካላት ጋር ለመምከር ያዘጋጀው መድረክ በአዳማ እየተካሄደ ነው።


 

በመድረኩ ላይ የፍትህ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ በላይሁን ይርጋ እንዳሉት ዜጎች በተለያዩ ምክንያቶች ሀገራቸውን ለቀው ወደ ተለያዩ ሀገራት ይፈልሳሉ።

በፍልሰቱም የመተላለፊያና የመዳረሻ ሀገራትን የፍልሰት ህጎችና አሠራሮች ባልተከተለና መደበኛ ባልሆነ መንገድ የህገወጥ መልማዮች፣ደላሎችና የተደራጁ የወንጀል ቡድኖች ሚና ከፍተኛ መሆኑን አንስተዋል።

ይህም ዜጎችን ለሞት፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለእንግልትና ለከፋ ሰብአዊ መብት ጥሰቶች እየዳረጋቸው መሆኑን  ጠቁመዋል።

ለችግሩ ምላሽ ለመስጠት ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው በተለይ ሰውን በሕገ ወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ከመታገል ጎን ለጎን ቀላል፣ መደበኛና ደህንነቱ የተረጋገጠ የውጭ ሀገር የስራ ስምሪትን የማስፋፋት ስራ በትኩረት መከናወን እንዳለበትም አስገንዝበዋል።

ህገ ወጥ ፍልሰትን ለመቀነስ ከሀገራዊ ኢኮኖሚ ሪፎርም ጋር አጣጥሞ ለማስኬድ የ10 አመት መሪ እቅድ መነደፉንም አክለዋል። 

በተለይ በሰው የመነገድና በሕገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን ለመከላከል ዓለም አቀፍ ስምምነቶችን ማጽደቅን ጨምሮ  የትብብር  አደረጃጀቶችን በመዘርጋት እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አቶ በላይሁን አብራርተዋል።

በፍትህ ሚኒስቴር የብሄራዊ የፍልሰት ትብብር ጥምረት ሴክሬታሪያት ኃላፊ አቶ አብርሃም አያሌው በበኩላቸው ባለፈው በጀት ዓመት በሰው የመነገድና ሰውን በህገወጥ መንገድ ድንበር የማሻገር ወንጀሎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ በርካታ ስራዎች መከናወናቸውን ገልጸዋል።


 

በዚሁ ህግ የማስከበር ስራ 600 የሚጠጉ ግለሰቦች በህገወጥ የሰዎች ዝውውር ተከሰው ከ10 እስከ 25 ዓመት የእስር ቅጣት እንደተፈረደባቸው ተናግረዋል።

የስደት ተጎጂዎችን ጥበቃና መልሶ በማቋቋም ረገድም ከ90 ሺህ በላይ ዜጎችን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉን ተናግረዋል።

ባለፈው በጀት ዓመት የኢኮኖሚ ፍልሰተኞችን ለመታደግም ለ504 ሺህ ዜጎች የውጭ አገር የሥራ እድል መፍጠር መቻሉን አውስተዋል።

በዓለም ዓቀፉ የህፃናት አድን ድርጅት በኢትዮጵያ መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ፕሮግራም አስተባባሪ አቶ ኃይለየሱስ ፀሐይ፤ ድርጅቱ በህዝብ ላይ ችግር እየሆነ የመጣውን መደበኛ ያልሆነ ፍልሰት ለመታደግ መንግሥት የሚያደርገውን ሁለንተናዊ ጥረት እየደገፈ መሆኑን ገልጸዋል።


 

በተለይ ህጻናት በፍልሰቱ እንደሚጠቁና ለችግር እንደሚጋለጡ ጠቁመው ህጻናቱን ከዚህ ችግር ለማላቀቅ የሚሰሩ ስራዎችን ከማጠናከርና ከመደገፍ አንፃር ፕሮግራሙ የክትትልና የአቅም ግንባታ ስራ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አብራርተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም