የክልሉ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እያበቃ ነው - ኢዜአ አማርኛ
የክልሉ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እያበቃ ነው

ጭሮ ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፦የኦሮሚያ ክልል መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እያበቃ መሆኑ ተገለጸ።
በምዕራብ ሐረርጌ ዞን ከ2 ቢሊዮን ብር በላይ ወጪ የተገነባው የጎሎልቻ የመስኖ ግድብ የፌዴራል እና የኦሮሚያ ክልል ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ዛሬ ተመርቋል።
በምረቃ ስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት በብልፅግና ፓርቲ የኦሮሚያ ክልል ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ ከፍያለው ተፈራ እንደገለጹት የክልሉ መንግስት የህዝቡን ተጠቃሚነት የሚያሳድጉ የልማት ፕሮጀክቶች በብዛትና በፍጥነት በማጠናቀቅ ለአገልግሎት እያበቃ ነው።
በዚህም በክልሉ ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ የተጀመሩ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን በፍጥነትና በጥራት በመገንባት ለማጠናቀቅ እንደተቻለም አመልክተዋል።
ለአገልግሎት የበቁ የመሰረተ ልማት ፕሮጀክቶችም የህዝቡን ተጠቃሚነት በማሳደግ የብልጽግና ጉዞን ለማረጋገጥ የሚያግዙ ናቸው ብለዋል።
ህብረተሰቡም የልማት ፕሮጀክቶችን በመጠበቅና በመንከባከብ የበኩሉን ሚና መወጣት እንዳለበት አመልክተዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የጎሎልቻ መስኖ ግድብም በክልሉ በመገንባት ላይ ካሉ 73 የመስኖ ፕሮጀክቶች አንዱና ትልቁ እንደሆነ ተናግረዋል።
የክልሉ መስኖና አርብቶ አደር ቢሮ ሀላፊ ኢንጂነር ግርማ ረጋሳ በበኩላቸው በክልሉ በግንባታ ላይ ከሚገኙ የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ውስጥ ግማሽ የሚሆኑት ተጠናቀው ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመራቸውን አስታወቀዋል።
በክልሉ ዝናብ አጠር አካባቢዎች ካለፉት አምስት አመታት ወዲህ 73 የመስኖ ፕሮጀክቶች በግንባታ ላይ መሆናቸውን ጠቁመው አብዛኞቹም በምዕራብ ሐረርጌና ቦረና ዞኖች አርብቶ አደር አካባቢዎች እየተገነቡ እንደሚገኙ ገልፀዋል።
ከእነዚህም 33 የሚሆኑት ሙሉ ለሙሉ ተጠናቀው አገልግሎት መጀመራቸውን ጠቁመው የተቀሩትን የመስኖ ግድብ ፕሮጀክቶች ፍጥኖ ለማጠናቀቅ ርብርብ እየተደረገ ነው ብለዋል።
በዛሬው ዕለት የተመረቀው የጎሎልቻ መስኖ ግድብ በአካባቢው ለሚገኙ 2 ሺህ በላይ አባወራ ቤተሰቦችን የሚያገለግል እና አንድ ሺህ ሄክታር በላይ መሬት የማልማት አቅም እንዳለው አመልክተዋል፡፡
የምዕራብ ሐረርጌ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ወይዘሮ ኢክራም ጠሀ በበኩላቸው መንግስት በዞኑ ዝናብ አጠር አካባቢዎች የገነባቸው የመስኖ ፕሮጀክቶች የህብረተሰቡን አኗኗር እየለወጡ ነው ብለዋል።
አርብቶ አደሩ በአንድ ቦታ ተረጋግቶ እንዲኖርና በግብርናው በስፋት እንዲሳተፍ እያደረገ መሆኑንም አመልክተዋል።
በዞኑ የሌሎች ሶስት የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ በፍጥነት እንዲጠናቀቅ የዞኑ አስተዳደር ያልተቋረጠ ድጋፍ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በቦርዶዲ ወረዳ ጎሎልቻ ቀበሌ አርብቶአደሮች በሰጡት አስተያየት የግድቡ መገንባት ለእንስሳት ውሀ ፍለጋ የሚሄዱትን ረጅም ርቀት አስቀርቶላቸዋል።
መንግስት የአርብቶአደሩን ችግር በመረዳት እያደረገላቸው ላለው ድጋፍ አመስግነዋል።