ቀጥታ፡

በመስከረም ወር ለሚከበሩ የህዝብና የአደባባይ በዓላት አስፈላጊው ዝግጅት ተጠናቋል-የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፦በመስከረም ወር የሚከበሩ የህዝብና የአደባባይ በዓላት በድምቀት እንዲከበሩ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን የባህልና ስፖርት ሚኒስቴር ገለፀ።

የባህልና ስፖርት ሚኒስትር ዴኤታ ነፊሳ አልማህዲ በመስከረም ወር የሚከበሩ የህዝብ በዓላት አከባበርን አስመልክቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸውም በመስከረም ወር የሚከበሩ በርካታ የህዝብና የአደባባይ በዓላትን በደመቀና በተሳካ ሁኔታ ለማክበርና ለማስተዋወቅ የሚያስችሉ ዝግጅቶች ተደርገዋል ብለዋል።

እነዚሁ የህዝብ በዓላት ሀገራዊ እድገትን ለማምጣት እና የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጠናክሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

በመስከረም ወር ከሚከበሩ የህዝብና የአደባባይ በዓላት መካከል የመስቀል ደመራ እና የኢሬቻ በዓላትን ጨምሮ የብሔር ብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት እንደሚገኙበት ተናግረዋል፡፡

ባህልና ስፖርት ሚኒስቴር የህዝብ በዓላቱን በማልማትና በማስተዋወቅ እሴታቸው ተጠብቆ በድምቀት እንዲከበሩ እየሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በዓላቱ ማህበራዊ መስተጋብርን የሚያጠናክሩ ወሳኝ የህዝብ ኩነቶች በመሆናቸው ለስኬታማነታቸው በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

ሁሉም ክብረ በዓላት፤ ባህላዊና ሃይማኖታዊ ይዘታቸውን ሳይለቁ የማህበረሰቡን አብሮነት በሚያጠናክር መልኩ ማክበር እንደሚገባ ነው ሚኒስትር ዴኤታዋ የተናገሩት፡፡

ክብረ በዓላቱን በሀገር አቀፍ፥ በአህጉር አቀፍ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በማስተዋወቅ ሀገራዊ ገፅታን ለመገንባት ከመገናኛ ብዙሃን ብዙ ስራ እንደሚጠበቅ ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም