ቀጥታ፡

ባለፉት ዓመታት በክልሉ የቱሪዝም ሀብትን በማስተዋወቅ ረገድ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፦ በኦሮሚያ ክልል ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ሀብትን በማስተዋወቅ በርካታ ስኬቶች መመዝገባቸውን የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን አስታወቀ።

የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ከመስከረም 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም እንደሚካሄድ  ተገልጿል።

የዘንድሮውን የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት አከባበር አስመልክቶ ኮሚሽኑ ዛሬ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የኦሮሚያ ክልል ቱሪዝም ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ነጋ ወዳጆ፤ በክልሉ ባለፉት አምስት ዓመታት የቱሪዝም ሃብቶችን በማስተዋወቅና በዘርፉ ግንዛቤ በመፍጠር ረገድ በተሰራ ስራ በርካታ ስኬቶች ተመዝግበዋል ብለዋል።

በተለይም ህብረተሰቡ ዘንድ በዘርፉ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ እንዲቻል ኮሚሽኑ በዓይነቱ ለየት ያለ የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንትን በዓመት አንድ ጊዜ ሲያዘጋጅ መቆየቱን ገልጸዋል።

ዘንድሮም ከመስከረም 20 እስከ 22 ቀን 2018 ዓ.ም ለአምስተኛ ዙር የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት የፌዴራልና የክልል መንግስት ኃላፊዎች እና በርካታ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ሀገር እንግዶች በሚገኙበት በአዲስ አበባ ስካይላይት ሆቴል ለማካሄድ አስፈላጊው ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል። 

የኦሮሚያ ቱሪዝም ሳምንት ዓላማ የባህልና ቱሪዝም ሀብትን በማስተዋወቅ እና በሀገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ባለድርሻ አካላት ዘንድ ጠንካራ ትብብርና ትስስር መፍጠር ነው ብለዋል።

በተጨማሪም ኢንቨስትመንትን መሳብና በቱሪዝም ዘርፍ ዘላቂ ልማት እንዲኖር ማስተዋወቅ፣ የባህል ዲፕሎማሲ የማሳደግ ዓላማ እንዳለው ተናግረዋል።

ዝግጅቱ ላይ በኦሮሚያ ቱሪዝም ዘርፍ የላቀ አስተዋፅኦ ላበረከቱ አካላት የኦሮሚያ ቱሪዝም ሽልማት የሚሰጥ ሲሆን፣  ለአንድ ዓመት አምባሳደር ሆና የክልሉን የቱሪዝም ሀብቶች የምታስተዋውቅ  'ሚስ ቱሪዝም ኦሮሚያ 2018' ውድድርም በደማቅና ባማረ መልኩ እንደሚካሄድ ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ቱርዝም ሳምንት ላይ የቱሪዝም ፎረም፣ የባህል ዐውደ ርዕይን ጨምሮ ሌሎች መርሃ ግብሮች እንደሚካሄዱም ምክትል ኮሚሽነሩ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም