ቀጥታ፡

የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን አፍሪካ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች የመሪነት ሚና እንድትጫወት የሚያስችላት ነው 

አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፦በሁለተኛው የአፍሪካ አየር ንብረት ጉባኤ የጸደቀው የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች የመሪነት ሚና እንድትጫወት የሚያስችላት መሆኑን የፕላን እና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር)ገለጹ

የፕላንና ልማት ሚኒስቴር ከአፍሪካ ህብረት ጋር በመተባበር ያካሄደው ሁለተኛውን የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አፈፃፀምና የተገኙ ውጤቶችን አስመልክተው የፕላንና ልማት ሚኒስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) ለመገናኛ ብዙሀን ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥተዋል።

በመግለጫቸው ጉባኤው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ ተጎጂ ብቻ ሳትሆን የመፍትሄ አካል መሆኗን ያሳየችበት ነው ብለዋል።

በተጨማሪም በጉባዔው አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን ለመፍታት ግንባር ቀደም ሚና እየተጫወተች መሆኑን ማስገንዘብ መቻሉን አመላክተዋል።

ጉባኤው የአፍሪካን የጋራ ድምጽ የያዘው የአዲስ አበባ ዲክላሬሽን በማጽደቅ መጠናቀቁን ጠቅሰው ዲክላሬሽኑ አፍሪካ በዓለም አቀፍ ደረጃ በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳዮች የመሪነት ሚና እንድትጫወት  የሚያስችላት መሆኑን ተናግረዋል። 

ለአፍሪካ የተሰጠውን ያልተገባ ትርክት በመቀየር እየወሰደቻቸው ያሉ ተጨባጭ እርምጃዎችን ማሳወቅ መቻሉን ተናግረዋል።

ይህም በአፍሪካ መሪዎችና ባስተላለፏቸው ውሳኔዎች በጉልህ መመላከቱን ገልጸዋል። 

ለአብነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በጉባኤው የመክፈቻ ንግግራቸው  አፍሪካ የምትፈልገው እርዳታና ችሮታ ሳይሆን ኢንቨስትመንት እንደሆነ  መግለጻቸውን አስታውሰዋል።  

የአረንጓዴ ማዕድናት እና ንጹህ የኢነርጂ ተደራሽነት የሚያሰፉ ስትራቴጂዎችን ማጠናከር ሌላኛው ጉባኤው ከስምምነት ላይ የደረሰበት አጀንዳ መሆኑን ጠቁመዋል።

በመሪዎች የተደረጉ ውሳኔዎችን በተመለከተም የአፍሪካ መሪዎች የሚሽን 300 አጀንዳ እና ክሊን ኩኪንግ ኢኒሼቲቭ  ተግባራዊ እንዲደረግ ማሳሰባቸውን ገልጸዋል።

እንዲሁም አፍሪካ ከአለም አቀፍ የታዳሽ ሃይል ኢንቨስትመንቶች ድርሻ በ2030 ከነበረበት ከ2 በመቶ  ወደ 20 በመቶ እንዲያድግ መጠየቃቸውን ጠቁመዋል፡፡

የአፍሪካ ህብረት የአረንጓዴ ማዕድን ስትራቴጂ ትግበራን ማፋጠን እንደሚገባ መወሰናቸውንም አንስተዋል።

ከአየር ንብረት ጋር የተገናኙ የጤና ስጋቶች እና በውሃ ወለድ የሚተላለፉ በሽታዎች ስርጭትን ለመፍታት መሪዎች የፋይናንስ ስርዓት ለመመስረት ቃል መግባታቸውን ጠቁመዋል።

በርካታ የጎንዮሽ ሁነቶች መካሄዳቸውን ገልጸው፤ ዓለም አቀፍ አጋሮች የፋይናንስ ድጋፎችን ለማድረግም ቃል መግባታቸውን ተናግረዋል።

በጉባኤው ኢትዮጵያ  የአየር ንብረት ተጽዕኖን መቀነስ ላይ የመሪነት ሚናዋን ለዓለም ማሳየቷን ገልጸው፤ የአረንጓዴ አሻራ መርሀ ግብር  የአዲስ አበባው ዲክላሬሽን ላይ ለአፍሪካ በሞዴልነት መጠቀሱን አንስተዋል።

በተጨማሪም የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ሳምንት በአዲስ አበባ መካሄዱን አስታውሰዋል።

ይህም በመልካም ሁኔታ መካሄዱን እና በዚህም ላይ ኢትዮጵያ በአየር ንብረት ለውጥ ምላሾች ላይ ተሞክሮዋን በስፋት ማካፈሏን ተናግረዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም