ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ ማሳያ ነው - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያ የከፍታ ጉዞ ማሳያ ነው
ጅግጅጋ፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለውጤት መብቃት የኢትዮጵያ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ ነው ሲሉ የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሻፊ አህመድ ገልጸዋል።
"በሕብረት ችለናል" በሚል መሪ ሐሳብ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ መጠናቀቁን አስመልክቶ በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ ሕዝባዊ የድጋፍና የደስታ መግለጫ ሰልፍ ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድን ጨምሮ ሌሎች የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች፣ የሀገር ሽማግሌዎችና የተለያዩ የሕብረተሰብ ክፍሎች ተሳትፈዋል።
የጅግጅጋ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ኢንጂነር ሻፊ በዚሕ ወቅት ባስተላለፉት መልዕክት፤ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ስኬት የኢትዮጵያ የከፍታና የማንሰራራት ጉዞ ማሳያ ነው ብለዋል።
ግድቡ የኢትዮጵያን የብልፅግና ስኬት አይቀሬነት ያረጋገጠ ነው ሲሉም ገልጸዋል።
ከሕዳሴው ቀጥሎ ብዙ ፕሮጀክቶች የሚጠበቁብን በመሆኑ እንደ ሕዳሴ በስኬት በማጠናቀቅ የኢትዮጵያን ማንሰራራት እውን እናደርጋለን ነው ያሉት።
የከተማው ሕዝብ ለግድቡ ግንባታ ሁለንተናዊ ድጋፍ ሲያደርግ መቆየቱን አስታውሰው፤ በቀጣይም ግዙፍ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች እንዲሳኩ ተሳትፎውን እንዲያጠናክር ጥሪ አቅርበዋል።
በሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፉ ላይ የተገኙት ገራድ ኩልምዬ ገራድ መሐመድ በበኩላቸው፤ የሕዳሴ ግድብ በሕብረት በመቆም ትልቅ ልማት ማሳካት እንደምንችል ያሳየንበት ነው ብለዋል።
የግድቡ ግንባታ ስኬት ሀገራዊ ልማትና እድገታችንን ለማፋጠን ይበልጥ የሚያነሳሳ ነው ሲሉም ተናግረዋል።