የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ቴክኖሎጂን በቀላሉ ለመላመድ አግዞናል - የስልጠናው ተሳታፊዎች - ኢዜአ አማርኛ
የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና ቴክኖሎጂን በቀላሉ ለመላመድ አግዞናል - የስልጠናው ተሳታፊዎች

ባህር ዳር፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠና የፈጠራ ስራን የበለጠ ለማዳበርና ቴክኖሎጂዎችን በቀላሉ ለመለማመድ እድል እንደፈጠረላቸው ስልጠናውን የወሰዱ የባህር ዳር ፖሊ ቴክኒክ ኮሌጅ መምህራን ገለጹ።
የኮሌጁ የኢንፎርሜሽን ቴክኖሎጂ መምህር ልጅዓለም መንግስት ለኢዜአ እንደገለጹት፤ ስልጠናው የፈጠራ አቅምንና አማራጭ የስራ ዕድሎችን ማስፋት የሚያስችል ነው።
ስልጠናው በበይነመረብ የሚሰጥና የዘመኑ ዲጂታል ቴክኖሎጂ የደረሰበትን ነባራዊ ሁኔታ ለማስገንዘብና የበለጠ ለማወቅ ተነሳሽነትን የፈጠረ ነው ብለዋል።
መተግበሪያዎችን በራስ አቅም መፍጠር የሚያስችል ክህሎት እና እውቀት የሚያስጨብጥና የአስተሳሰብ አድማስን ለማስፋት ጠቀሜታው የጎላ መሆኑን አንስተዋል።
ስልጠናው ፋንዳሜንታል ፕሮግራሚንግ፣ አንድሮይድ ዴቭሎፕመንት፣ አርቲፊሻል ኢንተሊጀንስ እና መሰል ዘመኑ የሚጠይቀውን የዲጂታል ቴክኖሎጂ ዕውቀት እና ክህሎት የሚያስጨብጡ ርዕሰ ጉዳዮች የተካተቱበት መሆኑን ተናግረዋል።
ስልጠናው በቦታ ሳይገደቡ እጅ ላይ ባለ ስልክ ሳይቀር የሚሰጥ በመሆኑ የዕድሉ ተጠቃሚ መሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የኮሌጁ ትምህርትና ስልጠና ምክትል ዲን ባንታየሁ ስንቴ በበኩላቸው፤ ስልጠናው ዓለም አቀፍ ቴክኖሎጂዎችን ለመረዳትና የበለጠ አስፍቶ ለማሰብ የሚያግዝ በመሆኑ የቴክኒክና ሙያ ኮሌጅ መምህራን አቅማቸውን ለማጎልበት ይህን እድል ፈጥነው መጠቀም ይገባቸዋል ብለዋል።
የባህር ዳር ከተማ አስተዳደር ስራና ስልጠና መምሪያ ኃላፊ ዘመነ አሰፋ እንዳሉት፤ ወጣቱ የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናን በመከታተል ከዲጂታል ገበያው ተጠቃሚ እንዲሆን በትኩረት እየተሰራ ነው።
ባለፈው ዓመት ለ7ሺህ 596 ወጣቶች ስልጠናውን ለመስጠት ታቅዶ ወደ ስራ እንደተገባ ገልጸው 7ሺህ 652 ወጣቶችን የስልጠናው ተጠቃሚ በማድረግ ከዕቅድ በላይ ማሳካት መቻሉን አስረድተዋል።
የዲጂታል ኢኮኖሚው ስርዓት እየፈጠነ በመሆኑ ዓለም አቀፍ አማራጮችን ለማስፋት የኢትዮ-ኮደርስ ስልጠናን መጠቀም ወቅቱ የሚጠይቀውን እውቀት ለመገብየት ያስችላል ብለዋል።
በተያዘው በጀት ዓመት ከ8ሺህ በላይ ወጣቶች የእድሉ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም አስታውቀዋል።