በክልሉ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ዝግጅት ተደርጓል - የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቁ ዝግጅት ተደርጓል - የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን
ሆሳዕና፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚከበሩ የአደባባይ በዓላት በሰላም እንዲጠናቀቅ ዝግጅት በማድረግ ወደ ተግባር መግባቱን የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ።
በኮሚሽኑ የወንጀልና ትራፊክ አደጋ መከላከል ቁጥጥር ዘርፍ ረዳት ኮሚሽነር አብርሃም ቲርካሶ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በክልሉ በሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች ዘንድ በዘመን መለወጫነት በርካታ የአደባባይ በዓላት ከዛሬ ጀምሮ ይከበራሉ።
በሀድያ ያሆዴ፣በከንባታ መሳላ፣መስቀል በጉራጌን ጨምሮ በክልሉ በሚገኙ ብሔር ብሔረሰቦች በስፋትና በድምቀት እንደሚከበርም ለአብነት አንስተዋል፡፡
የክልሉ ተወላጆችና የተለያዩ የህብረሰተብ ክፍሎች በዓላቱን ለማክበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ክልሉ እንደሚገቡም አስረድተዋል፡፡
በዓላቱ በርካታ ህዝብ በተሰበሰበበት በአደባባይ የሚከበሩ ሲሆኑ በሰላም እንዲጠናቀቁ ለማድረግ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ወደ ተግባር መግባቱንም አስረድተዋል፡፡
የከምባታ ብሔረሰብ ዘመን መለወጫ የሆነው የመሳላ በዓል ዛሬና ነገ የአካባቢው ተወላጆች፣ ወዳጆችና ተጋባዥ የክብር እንግዶች በተገኙበት በድምቀት እንደሚከበር ጠቁመዋል።
በዓሉ ያለ ምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበር የጸጥታ ማስከበር ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
በክልሉ በሌሎች ብሄሔር ብሐረሰቦች ዘንድ በዘመን መለወጫነት በአደባባይ የሚከበሩ በዓላት ያለምንም የጸጥታ ችግር እንዲከበሩ ተገቢው ቅድመ ዝግጅት መደረጉንም ጠቁመዋል።
እንዲሁም በዓሉን ለማክበር ከተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ወደ ክልሉ የሚገቡ እንግዶችና ወደ ቤተሰቦቻቸው የሚንቀሳቀሱ ነዋሪዎች ከትራንስፖርት ስምሪት፣ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ጋር ተያይዞ አንግልት እንዳይገጥማቸው እየተሰራ ነው ብለዋል።
ኮሚሽኑ ከክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ጋር በቅንጅት እየሰራ እንደሚገኝ ጠቁመዋል፡፡
የትራፊክ ደንብና መመሪያን በሚተላለፉ አሽከርካሪዎች ላይ ተገቢውን ህጋዊ እርምጃ ኮሚሽኑ እንደሚወስድ ጠቁመው ህጉን በተግባር በማይተገብሩ የትራፊክ ፍሰት ተቆጣጣሪዎች ላይም እርምጃ ለመውሰድ መግባባት ላይ ስለመደረሱም ተናግረዋል።
በበዓላት አከባበር ሂደት ላይም ይሁን በትራንስፖርት ፍሰት ላይ የሚያጋጥሙ ህገወጥ እንቅስቃሴዎችን ለፖሊስ ጥቆማ በመስጠት በኩል የክልሉ ማህበረሰብ መተባበር እንዳለበትም አሳስበዋል።