በክልሉ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ለማጉላት ትኩረት ተደርጓል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ - ኢዜአ አማርኛ
በክልሉ የቱሪዝም መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ለማጉላት ትኩረት ተደርጓል - ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ሀዋሳ፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የቱሪዝም መስህቦችን በማልማትና በማስተዋወቅ ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ለማጉላት ትኩረት መደረጉን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ተናገሩ፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ከኢዜአ ጋር ባደረጉት ቆይታ እንደገለጹት በክልሉ የቱሪስት መዳረሻ ስፍራዎችን በማልማት ኢኮኖሚያዊ ፋይዳቸውን ለማጉላት በትኩረት እየተሰራ ነው፡፡
በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ/ር) ሃሳብ አመንጪነት የተጀመረውና የገበታ ለትውልድ ፕሮጀክት አካል የሆነው የቱሪስት መዳረሻ ስፍራ በተያዘው ዓመት እንደሚጠናቀቅም ገልጸዋል፡፡
አቶ ጥላሁን በማብራሪያቸው ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ዕምቅ አቅም እንዳለው አንስተው ይህን በማልማት የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ በዩኔስኮ የተመዘገቡ ሶስት ቅርሶችን ጨምሮ፣ ፓርኮች፣ የአባያና ጫሞ ሃይቆች፣ ታሪካዊና ሃይማኖታዊ ስፍራዎች እንዲሁም ህዝባዊ በዓላትን በማስተዋወቅ ከቱሪዝም ዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ መሰራቱን አንስተዋል፡፡
የቱሪስቶችን ቆይታ ለማራዘም የአገልግሎት ሰጪ ተቋማትን ቁጥር ከመጨመር ባለፈ የተገልጋዩን እርካታ ለማሳደግ የአቅም ግንባታ ስልጠና መሰጠቱን አንስተዋል።
በክልሉ የሚከበሩ የብሄረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት አብሮነትን ከማጠናከር ባለፈ ለቱሪዝም ኢንደስትሪው ጉልህ ሚና ማበርከታቸውን ተናግረዋል፡፡
የቱሪስት መዳረሻዎች ባህላዊና ተፈጥሯዊ ይዘታቸውን ጠብቀው የሚለሙበትን አቅም ለመፍጠር በአርባምንጭ የወንዝ ዳርቻና በወላይታ የዳሞታ ተራራ ላይ የተጀመረው ልማት በሌሎች ከተሞች የማስፋት ስራ ይከናወናል ብለዋል፡፡
የክልሉ ባህልና ቱሪዝም ቢሮ ኃላፊ ወይዘሮ ወይኒቱ መልኩ በበኩላቸው ክልሉ የብዝሃ ቋንቋ፣ ባህልና ታሪክ ባለቤት መሆኑ ለቱሪዝም ኢንዱስትሪው የራሱ አበርክቶ እንዳለው ተናግረዋል፡፡
በክልሉ በአደባባይ የሚከበሩ የብሔረሰቦች የዘመን መለወጫ በዓላት የህዝቦችን የእርስ በርስ ትስስር የሚያጠናክሩ ባህላዊ እሴቶችን የያዙ መሆናቸውንም ገልጸዋል፡፡
በመሆኑም ባህሉን ጠብቆ ከማቆየት ባለፈ ለቱሪስት መስህብነት በማዋል ከዘርፉ የሚገኘውን ገቢ ለማሳደግ በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡
በክልሉ በቅርስነት የተመዘገቡ የኮንሶ መልክዓ ምድር፣ የታችኛው ኦሞ ሸለቆና የጌዲኦ መልክዓ ምድርን ጨምሮ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማልማት ስራ በክልሉ መንግስት በትኩረት እየተሰራ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የቢሮ ኃላፊዋ አክለውም የወላይታ ጊፋታ፣ የጋሞ ዮ ማስቃላ፣ የጎፋ ጋዜ መስቃላና የሌሎችንም ብሔረሰቦች የአደባባይ በዓላት የህዝቡን የእርስ በርስ ትስስር በሚያጠናክር መልኩ ለማክበር ዝግጅት መጠናቀቁን ገልጸዋል፡፡