በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መግባት የሚያስችለንን የአካል ብቃትና የሥነ-ልቦና ዝግጅት አድርገናል - ኢዜአ አማርኛ
በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መግባት የሚያስችለንን የአካል ብቃትና የሥነ-ልቦና ዝግጅት አድርገናል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦ በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ መግባት የሚያስችላቸውን የአካል ብቃትና የሥነ-ልቦና ዝግጅት ማድረጋቸውን ከተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የተውጣጡ እጩ ታዳጊ ስፖርተኞች ገለጹ።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በየዓመቱ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ታዳጊዎችን ተቀብሎ በማሰልጠን ተተኪ ስፖርተኞችን የማፍራት ተልዕኮውን እየተወጣ ይገኛል፡፡
አካዳሚው በዘንድሮ ዓመት በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ታዳጊዎችን ለማሰልጠን በ2017 ዓ.ም በነሀሴ ወር በሁሉም የሀገሪቱ አካባቢዎች በመንቀሳቀስ የመጀመሪያውን ዙር የእጩ ሰልጣኞች ምልመላ ሲያካሂድ ቆይቷል።
የመጀመሪያውን ዙር ያለፉና በዚህ ዓመት ተቋሙን የሚቀላቀሉ ታዳጊዎችን ለመለየት ሁለተኛው(የመጨረሻው) ዙር ምልመላ መስከረም 7 ቀን 2018 ዓ.ም በኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ ተጀምሯል።
ኢዜአ አካዳሚውን በመቀላቀል ራሳቸውን በስፖርት ዘርፍ ብቁ ለማድረግና ሀገራቸውን ለማስጠራት የተዘጋጁ የመጨረሻ ዙር ታዳጊ ተወዳዳሪዎችን በነገ ተስፋቸው ዙሪያ አነጋግሯቸዋል።
ከታዳጊዎቹ መካካል ጌታሁን ጁፋር አንዱ ሲሆን ከልጅነቱ ጀምሮ ለአትሌቲክስ ስፖርት ያለውን ልዩ ፍላጎት በውጤት ለማጀብ እንቅስቃሴ ሲያደርግ መቆየቱን ተናግሯል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ በዚህ ዓመት ታዳጊዎችን ተቀብሎ ለማሰልጠን ያመቻቸውን እድል በመጠቀም ወደ ተቋሙ መግባት የሚያስችለውን እድል ለማግኘት ተገቢውን ቅድመ ዝግጅት በማድረግ እየተወዳደረ እንደሚገኝ ገልጿል።
ሌላኛዋ ታዳጊ ዝናቧ መንገሻ በበኩሏ በቦክስ ስፖርት የመጀመሪያውን ምልመላ በማለፍ ለመጨረሻው ምልመላ መዘጋጀቷን ገልጻለች።
ቦክስ የሚጠይቀውን መስፈርት ለማሟላት ተገቢውን ዝግጅት ማድረጓንም ተናግራለች።
በተቋሙ በስፖርት ባለሙያዎች የሚሰጠውን የስልጠና እድል ለማግኘት ውድድር እያደረገ እንደሚገኝ የተናገረው ደግሞ ታዳጊ ኬኦል ጊዲ ነው።
ታዳጊ ሶስና ወጋየሁ በበኩሏ በሩጫ ውጤታማ ለመሆን ከአሰልጣኟ ያገኘችውን ትምህርት በመውሰድ የተሻለ ስፖርተኛ ለመሆን መዘጋጀቷን ገልጻለች።
ታዳጊዎቹ መሰል የስፖርት አካዳሚ እንዲስፋፉ ጠይቀው በቀጣይም አካዳሚውን በመቀላቀል የራሳቸውንና የሀገራቸውን ስም በዓለም አቀፍ ደረጃ ለማስጠራት ዓላማ መሰነቃቸውን ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ ስፖርት አካዳሚ የትምህርትና ስልጠና ውድድር ምክትል ዋና ዳይሬክተር ደሳለኝ በላይ አካዳሚው በዚህ ዓመት 400 ታዳጊ ስፖርተኞችን ተቀብሎ ለአራት ዓመታት ለማሰልጠን መዘጋጀቱን ገልጸዋል።
አካዳሚው በእያንዳንዱ የስፖርት ዓይነት በቂ እውቀትና ልምድ ያላቸውን 130 መልማዮች በተለያዩ ክልሎች በማሰማራት ከነሀሴ 5 እስከ 30 ቀን 2017 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር እጩ ሰልጣኞችን መመልመሉን ጠቁመዋል።
ይህን ተከትሎ ከመስከረም 7 እስከ 11 ቀን 2018 ዓ.ም የመጀመሪያውን ዙር ካለፉ 550 እጩ ሰልጣኞች መካከል አካዳሚውን የሚቀላቀሉ 400 ታዳጊ ስፖርተኞችን የመለየት ስራ መጀመሩን ተናግረዋል።
ምልመላውን ያለፉ ታዳጊዎች ከመስከረም 27 ቀን 2018 ዓ.ም ጀምሮ በተለያዩ የስፖርት አይነቶች ስልጠናቸውን እንደሚጀምሩም አካዳሚው አስታውቋል።