ወላይታ ድቻ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ከሊቢያው አል-ኢትሃድ ጋር ዛሬ ያደርጋል - ኢዜአ አማርኛ
ወላይታ ድቻ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የማጣሪያ ጨዋታውን ከሊቢያው አል-ኢትሃድ ጋር ዛሬ ያደርጋል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018 (ኢዜአ)፦ ወላይታ ድቻ የ2025/26 የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ የመጀመሪያ ማጣሪያ ጨዋታውን ከሊቢያው አል-ኢትሃድ ጋር ዛሬ ያከናውናል።
የሁለቱ ቡድኖች ጨዋታ ከቀኑ 9 ሰዓት በአበበ ቢቂላ ስታዲየም ይካሄዳል።
ወላይታ ድቻ በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ኢትዮጵያን ወክሎ የሚሳተፈው የኢትዮጵያ ዋንጫ አሸናፊ መሆኑን ተከትሎ ነው።
በአሰልጣኝ ገብረክርስቶስ ቢራራ የሚመራው ቡድን በሶዶ እና አዳማ ከተሞች ዝግጅቱን ሲያደርግ ቆይቷል።
የሊቢያው አል-ኢትሃድ በሊቢያ ፕሪሚየር ሊግ አራተኛ መውጣቱን ተከትሎ የካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ተሳትፎን አግኝቷል።
በካፍ ኮንፌዴሬሽን ዋንጫ ወላይታ ድቻ ሲሳተፍ የአሁኑ ለሁለተኛ ጊዜ ነው።
እ.አ.አ በ2018 ተሳትፎ በመጨረሻው ዙር ማጣሪያ በታንዛንያው ያንግ አፍሪካንስ በደርሶ መልስ ተሸንፎ ወደ ምድብ ድልድል መግባት ሳይችል ቀርቷል።
በወቅቱ ወላይታ ድቻ በመጀመሪያው ዙር የታንዛንያውን ዚማሞቶ ሲያሸንፍ በሁለተኛው ዙር ባልተጠበቀ ሁኔታ የግብጹን ዛማሌክን በመጣል ወደ ሶስተኛ ዙር ማለፉ አይዘነጋም።
ወላይታ ድቻ እና አል-ኢትሃድ የመልስ ጨዋታቸውን መስከረም 16 ቀን 2018 ዓ.ም ያደርጋሉ።
ወላይታ ድቻ በደርሶ መልስ ውጤት ካሸነፈ በመጨረሻው ዙር ከግብጹ አል ማስሪ ጋር ይገናኛል።