ፎረሙ ከተሞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በጋራ በማልማት እንዲበለፅጉ ያስችላል - ኢዜአ አማርኛ
ፎረሙ ከተሞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በጋራ በማልማት እንዲበለፅጉ ያስችላል
አዲስ አበባ፤ መስከረም 9/2018(ኢዜአ)፦ የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም ከተሞች እርስ በእርስ እንዲተዋወቁና ያላቸውን ተፈጥሯዊ ፀጋዎች በጋራ በማልማት እንዲበለፅጉ የሚያስችል መሆኑን የከተማና መሰረተ ልማት ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ አስታወቁ፡፡
ሚኒስትር ጫልቱ ሳኒ ከአፋር ክልል መንግስት ጋር በመተባበር በሰመራ ሎግያ ከተማ "የከተሞች እድገት ለኢትዮጵያ ልህቀት" በሚል መሪ ሃሳብ ከህዳር 6 እስከ 10 ቀን 2018 ዓም የሚካሄደውን 10ኛው የኢትዮጵያ ከተሞች ፎረም በማስመልከት መግለጫ ሰጥተዋል።
ሚኒስትሯ በመግለጫቸው የከተሞች ፎረም በኢትዮጵያ ከ2002 ዓ.ም ጀምሮ በየሁለት ዓመቱ ሲካሄድ መቆየቱን ጠቅሰው ዓላማውም በከተሞች መካከል የትብብር መንፈስን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ተናግረዋል።
በተጨማሪም ወንድማማችነትን በማጎልበት ፉክክርን ማዕከል ያደረገ የስራ ባህልን እንደሚያሳድግ ነው በመግለጫቸው ያመላከቱት።
ፎረሙ ከተሞች ያላቸውን የኢንቨስትመንት፣ የንግድና የቱሪዝም አቅም የሚያንጸባርቁበት እንደሆነም ጨምረው ገልጸዋል።
በመርሃ ግብሩ 150 ከተሞች ተመዝግበው የሚወክሏቸውን አካላት እንደለዩና ከ10 በላይ የንግድ ድርጅቶች እንደሚሳተፉ ሚኒስትሯ አስታውቀዋል።
በፎረሙ ኤግዚቢሽንና በተለያዩ መስኮች የተከናወኑ ጥናታዊ ፅሁፎች የሚቀርቡ ሲሆን በከተማ ልማት ፖሊሲ ዙሪያ ውይይት እንደሚደረግም ጠቁመዋል፡፡