ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው ያለንን ተሰሚነት ያሳደገ ዘመን ተሻጋሪ ስኬት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ - ኢዜአ አማርኛ
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው ያለንን ተሰሚነት ያሳደገ ዘመን ተሻጋሪ ስኬት ነው - ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ
ጅግጅጋ፤ መስከረም 09/2018(ኢዜአ)፦ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ በቀጣናው ያለንን ተሰሚነት ያሳደገ ዘመን ተሻጋሪ የስኬት ማህተም ያረፈበት ፕሮጀክት ነው ሲሉ የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ ተናገሩ።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ተጠናቆ መመረቁን በማስመልከት በሶማሌ ክልል ጅግጅጋ ከተማ እና በተለያዩ የክልሉ ከተሞች የድጋፍ ሰልፍ በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በጅግጅጋ እየተካሄደ ባለው የድጋፍ ሰልፍ ላይ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሐመድ ባስተላለፉት መልዕክት ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ሁሉንም ያስተሳሰረና አንድነትን ያጠናከረ ፕሮጀክት መሆኑን ገልጸዋል።
የግድቡ ግንባታ የመሰረት ድንጋይ ከተቀመጠበት እለት አንስቶ በተለይም የውሃ ሙሌት ከተጀመረ በኋላ በርካታ ፈተናዎች ያጋጠሙት ፕሮጀክት መሆኑን ያነሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ፈተናዎቹና ጫናዎቹ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ቆራጥ አመራርና በኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፍ ከዳር መድረሱን አውስተዋል።
ግድቡ የትውልድ አሻራ ያረፈበት የህብረታችን ማሳያ መሆኑን ያነሱት አቶ ሙስጠፌ፤ ዘመን ተሻጋሪ የልማት ስኬት ነውም ብለዋል።
እንደ ርዕሰ መስተዳደሩ ገለጻ ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ዘመን ተሻጋሪ የስኬታችን ማህተም ያረፈበት ፕሮጀክት ነው።
ከዚህም ባለፈ የግድቡ መጠናቀቅ በቀጣይ መንግስት የወጠናቸው ታላላቅ የልማት ፕሮጀክቶችን ለማሳካት ትልቅ መነሳሳትን የፈጠረ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይም የሶማሌ ክልል ፕሮጀክቶቹ ከሚከናወኑባቸው አካባቢዎች አንዱ በመሆኑ ህዝቡ ትኩረቱን ልማት ላይ ማድረግ አለበት ብለዋል።