በምዕራብ ጎንደር ዞን በአኩሪ አተር ከለማው መሬት ከአራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል - ኢዜአ አማርኛ
በምዕራብ ጎንደር ዞን በአኩሪ አተር ከለማው መሬት ከአራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይጠበቃል
ገንዳ ውሃ ፤ መስከረም 9/2017(ኢዜአ)፡- በምዕራብ ጎንደር ዞን በመኸሩ ወቅት በአኩሪ አተር ሰብል ከለማው መሬት ከአራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ የዞኑ ግብርና መምሪያ አስታወቀ።
በመምሪያው የሰብል ልማት ባለሙያ አቶ ቻላቸው አቸነፍ ለኢዜአ እንደገለጹት፤ በዞኑ የአኩሪ አተር ሰብል ምርታማነትና በገበያም አዋጪነት ያለው ነው።
በልማቱም ከ48 ሺህ በላይ አርሶ አደሮችና 526 ባለሃብቶችን በማሳተፍ ከ148 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በአኩሪ አተር ሰብል መሸፈን መቻሉን ተናግረዋል።
ከለማው መሬት ውስጥ ከ34 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነው መሬት በባለሃብት፤ ቀሪው ደግሞ በአርሶ አደር መሆኑን አስረድተዋል።
በሰብሉ ከለማው መሬትም ከአራት ነጥብ ሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠበቅ አስታውቀዋል።
ይህም ለኢንዱስትሪዎች ግብአትና ወደ ውጭ በመላክ የውጭ ምንዛሪ ግኝትን ለማስፋት እንደሚያግዝ ገልጸዋል።
በዞኑ የገንዳ ውኃ አካባቢ አርሶ አደሮች መካከል አቶ አህመድ ሙስጦፋ እንደተናገሩት፤ የአኩሪ አተር ሰብል በገበያ አዋጪነቱና ምርታማነቱ እያደገ በመምጣቱ ሶስት ሄክታር መሬታቸው በአኩሪ አተር አልምተዋል።
ካለሙት የአኩሪ አተር ሰብልም ከ70 ኩንታል በላይ ምርት እንደሚጠብቁ ገልጸዋል።
ከ100 ሄክታር መሬት ላይ ያለሙት የአኩሪ አተር ሰብል አሁን ላይ በጥሩ ቀመና ላይ እንደሚገኝ የተናገሩት ደግሞ በመተማ ወረዳ በእርሻ ኢንቨስትመንት የተሰማሩት የባለሃብት ተወካይ አቶ ፀጋው አደራጀው ናቸው።
ባለፈው ዓመት 40 ሄክታር መሬት በማልማት ከ100 ኩንታል በላይ ምርት ያገኙ መሆኑን አስታውሰው፤ በዚህ ዓመት 300 ኩንታል ምርት ይገኛል ተብሎ ይጠበቃል ብለዋል።
በመኸሩ ወቅት የዝናብ ስርጭት ለአኩሪ አተር ሰብል ምቹ መሆኑና አስፈላጊውን የምርት ማሳደጊያ ግብዓት መጠቀም መቻላቸው የተሻለ ምርት እንደሚጠብቁ ተናግረዋል።
ከግብርና መምሪያው የተገኘው መረጃ አንደሚያመለክተው፤ በምዕራብ ጎንደር ዞን ባለፈው ዓመት በአኩሪ አተር ከለማው 140ሺህ 700 ሄክታር መሬት ላይ ከሶስት ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ተሰብስቧል።