ቀጥታ፡

ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ የኢትዮጵያን የኒውክሌር ቴክኖሎጂ የመጠቀም እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ ገለጸ

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018 (ኢዜአ)፦ዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለመጠቀም የጀመረችውን እንቅስቃሴ እንደሚደግፍ ገልጿል።

የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በቪየና ኦስትሪያ እየተካሄደ ካለው 69ኛው የIAEA መደበኛ ጉባኤ ጎን ለጎን ከዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር ራፋኤል ማርያኖ ግሮሲ ጋር የሁለትዮሽ ውይይት አድርገዋል፡፡

ውይይቱ ኢትዮጵያ በምታካሂደው ሰላማዊ የኒውክሌር ኃይል ፕሮግራም በሰው ኃይል አቅም ግንባታ እና በሌሎች ጉዳዮች ዙሪያ የዓለም አቀፉ አቶሚክ ኢነርጂ ኤጀንሲ ስለሚያደርጋቸው ድጋፎች ያተኮረ ነው።

በለጠ ሞላ (ዶ/ር) በዚህ ወቅት÷ የኤጀንሲው ዋና ዳይሬክተር ለኢትዮጵያ የካንሰር ማከሚያ መሳሪያ ድጋፍ ማድረጋቸውን አመስግነው፤ የሰው ኃይል አቅም ግንባታ ላይ ኤጀንሲው የተጠናከረ ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

ኢትዮጵያ የሰላማዊ ኒውክሌር ኢነርጂ ፕሮግራሞችን እውን ለማድረግ መሠረት በመጣል ላይ መሆኗን እና ወደ ትግበራ ለመግባትም ሰፊ ጥረት እያደረገች መሆኗን አብራርተዋል።

በዚህም ብሄራዊ የኒውክሌር ኃይል ግንባታ ላይ የቴክኒክ ድጋፍ እና የእውቀት ሽግግር ማድረግ ወሳኝ በመሆኑ ኤጀንሲው ድጋፍ እንዲያደርግ ጠይቀዋል፡፡

በኢትዮጵያ በግብርና እና ጤና ዘርፍ የተጀመሩ ስራዎችን ስኬታማ ለማድረግ ከኤጀንሲው ከፍተኛ ድጋፍ እንደሚፈልጉም መግለፃቸውን ፋና ዲጂታል የሚኒስቴሩን ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ሥራ አስፈፃሚ አቶ ተስፋዬ ዓለምነውን ጠቅሶ ዘግቧል።

ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ ዓላማ ለመጠቀም የጀመረችውን የቁጥጥር ማዕቀፍ ለማጠናከር ጉልህ ሚና እየተወጣች መሆኗን የገለጹት ሚኒስትሩ ይህንንም በይበልጥ ለማጠናከር የኤጀንሲው ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አንስተዋል።

ራፋኤል ማርያኖ ግሮሲ በበኩላቸው በቅርቡ ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ጋር በተለያዩ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት ማድረጋቸውን ገልጸው ኢትዮጵያ የኒውክሌር ቴክኖሎጂን ለሰላማዊ መንገድ ለመጠቀም የጀመረችውን እንቅስቃሴ ኤጀንሲ እንደሚደግፍ አረጋግጠዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም