ቀጥታ፡

በቀጣዩ የዩኔስኮ ጉባዔ ጊፋታን በዓለም ቅርስነት ለማስመዝገብ እየተሠራ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018 (ኢዜአ)፡- የወላይታ ብሔር የዘመን መለወጫ በዓል (ጊፋታ) በዓለም አቀፍ ቅርስነት እንዲመዘገብ ለማድረግ የዝግጅት ተግባራት እየተከናወኑ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለስልጣን አስታወቀ።

የተባበሩት መንግሥታት የሣይንስ፣ ትምህርት እና ባህል ድርጅት (ዩኔስኮ) የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ጥበቃ ዓለም ዓቀፍ መንግሥታት ኮሚቴ 20ኛ ጉባዔ በፈረንጆቹ ከታኅሣሥ 8 እስከ 13 በሕንድ ኒውደልሂ ይካሄዳል።

በጉባዔው ጊፋታ በዩኔስኮ እንዲመዘገብ የሚያስችሉ የዝግጅት ሥራዎች እየተከናወኑ መሆኑን በባለስልጣኑ የቅርስ ምርምር መሪ ሥራ አስፈፃሚ ዮናስ ይልማ (ዶ/ር) ለኢዜአ ተናግረዋል።

እስካሁንም ቀደም ሲል በላክነው ሠነድ ላይ ከዩኔስኮ የማይዳሰስ ባህላዊ ቅርስ ገምጋሚ ኮሚቴ በተለያየ ጊዜ ለቀረቡልን ጥያቄዎች ምላሽ ሰጥተናል ብለዋል።

በዚህም መሠረት ከዩኔስኮ ሁለት ጊዜ ለቀረቡ ጥያቄዎች፤ የባህሉን ባለቤት (ከዋኝ) ማኅበረሰብ በማሳተፍ እና በማወያየት ምላሽ መስጠት መቻሉን ጠቅሰዋል።


 

ጥያቄዎቹን ለመመለስ ተሳታፊ የሆኑትም፤ በወላይታ ዞን የሚገኙ ሽማግሌዎች፣ ወጣቶች፣ ሴቶች እና የዞኑ የባህል ዘርፍ ባለሙያዎች መሆናቸውን አብራርተዋል።

ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በጉባዔው በመገኘት የምዝገባ ሂደቱን ለመከታታል ብሎም ለሚነሱ ጥያቄዎች ምላሽና ማብራሪያ ለመስጠት በአሁኑ ወቅት ዝግጅት እየተደረገ እንደሚገኝ አመላክተዋል።

መስቀል፣ ጥምቀት፣ ፊቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ሥርዓት፣ ሸዋል ዒድ እና ሄር-ኢሴ (የሶማሌ ኢሳ ማኅበረሰብ ያልተፃፈ ባህላዊ የዳኝነት ሥርዓት) በዓለም ቅርስነት መመዝገባቸውን አውስተዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም