ቀጥታ፡

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የግንባታ ሂደት በቀጣይ ለሚሠሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች አስተማሪ ነው

አዲስ አበባ፤ መስከረም 8/2018 (ኢዜአ)፡- ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ያለፈባቸው ሂደቶች በቀጣይ ለሚከናወኑ ሜጋ ፕሮጀክቶች ትምህርት እንደሚሰጥ የፕሮጀክቱ ዋና ስራ አስኪያጅ ክፍሌ ሆሮ(ኢ/ር) ገለጹ።

ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ለሐሩራማ የአየር ሁኔታ ባለመበገር 24 ሠዓት ሳይቋረጥ በከፍተኛ መስዋዕትነት የተገነባ መሆኑንም ለኢዜአ ተናግረዋል።

ሠራተኛው ስለተከፈለው ብቻ ሳይሆን ለሀገሬ ምን ላበርክት በሚል ቁርጠኝነትና ባለቤትነት ጭምር የገነባው መሆኑንም አንስተዋል።

የሀይድሮ ኤሌክትሪክ ፕሮጀክት በባሕሪው ሰፊና ውስብስብ አሠራርን ያካተተ የምህንድስና መስክ መሆኑን ገልጸው፤ ከዚህ ሰፊ ዘርፍ እንደ ሀገርም ሆነ እንደ ባለሙያ በርካታ ዕውቀት መቅሰም መቻሉን ገልጸዋል።

ምንም እንኳን ቀደም ሲል ከተሠሩ ፕሮጀክቶች በርካታ ዕውቀት የተገኘ ቢሆንም፤ በአንድ ተቋም ተደራጅተው ባለመያዛቸው ፕሮጀክቶቹ ሲጠናቀቁ ዕውቀቱም መበተኑን አውስተዋል።

ከዚህ አንጻር በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ የተገኘው ዕውቀትም የፕሮጀክቱን መጠናቀቅ ተከትሎ እንዳይበተን በተደራጀ አግባብ በማኖር ለቀጣይ ሥራ ዐቅም እንዲሆን ማድረግ ተገቢ ነው ብለዋል።

ይህን ታሳቢ በማድረግም የተገኘውን ዕውቀትና ልምድ በማሰባሰብ፤ የኮንስትራክሽን፣ የዲዛይንና የምህንድስና ኩባንያዎችን ለማቋቋም በመንግሥት በኩል እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን ጠቁመዋል።

በተገቢው መንገድ በጥናት ላይ የተመሰረተ የአቅም ግንባታ ከተከናወነ ኩባንያዎቹ ከሀገር አልፈው በውጪ ሀገር ደረጃ ተወዳዳሪ የሚሆኑበት ዕድል ሰፊ ስለመሆኑም አመላክተዋል።

የሕዳሴ ግድቡ አሠሪው፣ መሀንዲሱ፣ ባለሙያውና ሠራተኛው ለአንድ ግብ ቆመው የተገነባ በመሆኑ በቀጣይ ለሚሠሩ ሜጋ ፕሮጀክቶች በአርዓያነት የሚወሰድ በግብዓትነትም የሚጠቅም ፕሮጀክት ነው ብለዋል።

በአንድነት በርትቶ መቆም ከተቻለ የማይታለፍ ችግር እንደሌለ ጠቁመው በሕዳሴ ግድቡ ግንባታ ሂደት የተገኘው ልምድ ለቀጣይ ፕሮጀክቶችም አስተማሪ ነው ሲሉ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት
2015
ዓ.ም